ሀገር አቀፍ ለኤችአይቪ ምርመራና ህክምና የማስጀመር ንቅናቄ ይፋ ሆነ

የጤና ሚኒስቴር ሮታ ROTA (Replicate operation triple A) ከተሰኘ ድርጅት ጋር በመተባበር ለ6 ወራት የሚቆይ ለኤችአይቪ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን የመመርመርና ህክምና የማስጀመር ንቅናቄ ይፋ አድርጓል፡፡

ከፌዴራልና ከክልል የተውጣጡ አመራሮችና ፈፃሚ አካላት በተገኙበት አውደ ጥናት የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ድጉማ ኮቪድ- 19 ወረርሽኝ በጣም ከጎዳቸው አገልግሎቶች መካከል አንዱ ለኤችአይቪ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን የመመርመር ስራ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በእ.አ.አ  2020 ለመድረስ ከታቀደው 90 በመቶ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎችን የመመርመር እቅድ 79 በመቶ ብቻ እንደተከናወነ ጠቅሰው በቀጣይ 6 ወራት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የፌዴራል ኤችአይቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር ጄኔራል ዶ/ር ፅጌረዳ ክፍሌ በበኩላቸው፣ በቀደሙት አመታት በተገኘው መልካም ውጤትና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የታየው መዘናጋት ችግሩን አባብሶት መቆጣጠር ወደ ማይቻልበት ደረጃ ከመድረሱ በፊት በተለይ በምርመራና ልየታ ጠንካራ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡

በአዲስ አበባ የተገኘውን ምርጥ ተሞክሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋት የልምድ ልውውጥ ጉብኝት የተደረገ ሲሆን፣ ክልሎች ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ የ6 ወር ዕቅድ አውጥተው ውይይት መደረጉን ከጤና ሚኒስቴር  ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡