ባለፉት አምስት ዓመታት በማእድን ዘርፍ በትኩረት ተሰርቷል – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ሕዳር 14/2016 (አዲስ ዋልታ) ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ለመበልፀግ አምስት ዋና ዋና የትኩረት ዘርፎች ለይታ ስትሰራ የነበረ ሲሆን ከዚህ ውስጥ አንዱ የማእድን ዘርፍ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለተኛውን ሀገር አቀፍ የማእድን እና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ በሚሊኒየም አዳራሽ መርቀው ከፍተዋል፡፡

ኤክስፖው ኢትዮጵያ ያላትን የማእድን ክምችት የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስችል ሁኔታ ላይ እንዳለች ማሳያ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገልጸዋል፡፡

በኤክስፖው መክፈቻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የፌደራል ተቋማት የስራ ኃላፊዎች፣ በማእድን ዘርፋ የተሰማሩ ባለሀብቶች፣ አምባሳደሮች እንዲሁም የክልል ቢሮ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

ከ90 በላይ ኩባንያዎች በኤክስፖው ተሳታፊ ሲሆኑ የወርቅ፣ የድንጋይ ከሰል፣ የከበሩ ማእድናት ጌጣጌጦች እንዲሁም የኢንዱስትሪ ማእድን ቴክኖሎጂ ሲሚንቶና ብረት ይዘው ቀርበዋል።

ከህዳር 14 እስከ ህዳር 18/2016 በሚቆየው ኤክስፖ ጎን ለጎን ለ3 ቀናት የሚቆይ ምክክር ይኖራልም ተብሏል፡፡

በማዕድን ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች እና የሚመለከታቸው አካላት ልምድና ተሞክሯቸውን የሚያጋሩበት ስለመሆኑም ተነግሯል፡፡

በስመኝ ፈለቀ