ብልፅግና ፓርቲ በአዳማ የምርጫ ቅስቀሳ አካሄደ

ብልፅግና ፓርቲ በአዳማ ከተማ አባላትና ደጋፊዎቹ በተገኙበት የምርጫ ቅስቀሳ አካሄደ፡፡

በአዳማ ከተማ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አለማየሁ ቱሉ፣ ብልጽግና ትክክለኛውን ፌዴራልዝም እውን በማድረግ ሀገሪቱን ከድህነት ለማላቀቅና የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

አቶ አለማየሁ ፓርቲያቸው ቢመረጥ በሀገሪቷ እውነተኛ ፌዴራሊዝምን ለማረጋገጥ፣ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት የሚሠራ እና እየሠራ የሚገኝ ፓርቲ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሀይሉ ደልጁ በበኩላቸው ብልፅግና ፓርቲ ሀሳብ ተውሶ ወደ ስራ መድረክ የሚወጣ ሳይሆን አዳዲስ ሀሳቦችን በማፍለቅ ይሰራል ነው ያሉት።

ዘንድሮ የሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሠላማዊ ግልፅ እና ዲሞክራሳዊ እንዲሆን ሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ብልፅግና ፓርቲ ትናንትን እንደጨለማ ጊዜ መመልከት ሳይሆን መልካሙን በመውሰድ ድክመቶቹን የሚያርም ነው ሲሉ አቶ ሀይሉ ተናግረዋል።

ትናንት ድክመቶች ብቻ ሳይሆኑ አስደናቂ የሚባል ስኬቶች የተመዘገቡበት ጊዜም ነበር ብለዋል።

(በሚልኪያስ አዱኛ)