2021 የጤና እና ክብካቤ ባለሙያዎች ዓመት ተብሎ ተሰየመ

የዓለም የጤና ድርጅት የፈረንጆቹን 2021 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የጤና እና ክብካቤ ባለሙያዎች ዓመት ብሎ ባወጀው መሠረት፣ በኢትዮጵያም በዛሬው ዕለት በይፋ መጀመሩን ጤና ሚኒስቴር ገልጿል።
ዓለም አቀፍ የጤና እና ክብካቤ ባለሙያዎች ዓመት “መከላከል፣ ማልማት፣ እና አብሮነት” (Protect. Invest. Together) በሚል መሪ ቃል የሚከበር መሆኑ ነው የተገለጸው።
ይህም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ለዘርፉ የሚያደርጉትን ኢንቨስትመንት እንዲያሳድጉ፣ የጤና ባለሙያዎች ለኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ቅድሚያ እንዲሰጣቸው፣ ምቹ እና ራሳቸውን ከአደጋ ለመካለከል የሚያስችል የሥራ ቦታ እንዲፈጠር እንዲሁም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ከጤና ባለሙያዎች ጎን እንዲቆም የተግባቦት ሥራዎች መስራት ላይ ያተኩራል ተብሏል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ዛሬ በተካሄደው የማስጀመሪያ መድረክ ባደረጉት ንግግር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ የጤና ባለሙያዎች የከፈሉትን ከፍተኛ መሥዋዕትነት እና ኅብረተሰቡን ለማገልገል ያሳዩትን ከፍተኛ ጥረት በማሰብ ተገቢውን ምስጋና እና ዕውቅና ለመስጠት 2021 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የጤና እና ክብካቤ ባለሙያዎች ዓመት ሆኖ ተሰይሟል ብለዋል።
በኢትዮጵያም የጤና ባለሙያዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር እና ምላሽ ለመስጠት በሚደረገው ጥረት ላይ ግንባር ቀደም የሆነ ሚና ሲጫወቱ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
በዚህም ወቅት ለኮቪድ 19 በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ከመሆናቸው አንጻር ተገቢው ራስን ከበሽታ የመከላከያ ቁሳቁስ በማቅረብ፣ በኮቪድ 19 ዙሪያ ሥልጠናዎችን በመስጠት፣ ለኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ቅድሚያ እንዲያገኙ በማድረግ እና ሌሎች ተመሳሳይ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይቷል ብለዋል።
ኅብረተሰቡም ከቫይረሱ ራሱን በመጠበቅ በባለሙያዎቹ ላይ ያለውን ጫና በመቀነስ ወረርሽኙን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት መደገፍ አለበት ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ ላይ ዓለም አቀፍ የጤና እና ክብካቤ ባለሙያዎች ዓመትን በይፋ ከማስጀመር በተጨማሪ በአገራችን የሚስተዋለውን የጤናው ዘርፍ የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ውልም የጤና ሚኒስቴር እና የተለያዩ የጤና ሙያ ማኅበራት መፈራረማቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።