ቦርዱ ከምርጫ ጣቢያዎች ጋር በተገናኘ ከአፋር ክልል የቀረበለትን አቤቱታ መርምሮ ውሳኔ እንደሚሰጥ አስታወቀ

 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

የካቲት 11/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከምርጫ ጣቢያዎች ጋር በተገናኘ ከአፋር ክልል የቀረበለትን አቤቱታ መርምሮ ውሳኔውን እንደሚሰጥ አስታወቀ፡፡

ቦርዱ ዛሬ በሰጠው አጭር መግለጫ የምርጫ ጣቢያዎቹ ዝርዝር ይፋ መሆንን ተከትሎ ከአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የምርጫ ጣቢያዎች ያለአግባብ በሶማሌ ብሔራዊ ክልል መንግስት ስር በሚገኙ ቀበሌዎች ስም ይፋ ተደርገዋል የሚል አቤቱታ እንደቀረበለት ገልጿል።

የአፋር ክልላዊ መንግስት በአቤቱታው በ8 ቀበሌዎች የሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎችን ዝርዝር በማቅረብ ማስተካከያ እንዲደረግ መጠየቁንም ነው በመግለጫው የጠቀሰው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ከአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የቀረበውን አቤቱታ በመመልከት የመራጮች ምዝገባ ከመጀመሩ በፊት መርምሮ ውሳኔውን እንደሚያሳውቅ ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ኛው አገራዊ ምርጫን የሚመለከቱ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነ ይታወቃል።

ከነዚህ ተግባራትም መካከል ስልጠናዎችን መስጠት፣ በክልሎች የምርጫ ክልል ቢሮዎችን መክፈት፣ እጩዎች መመዝገብ እና አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ለማህበረሰቡ ማቅረብ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

በመሆኑም በጊዜ ሰሌዳው መሰረት የካቲት 03 ቀን 2013 ዓ.ም በመላው ኢትዮጵያ ምርጫ የሚካሄድባቸው ምርጫ ጣቢያዎችን ዝርዝር ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡