ተመራማሪዎች የኮቪድ-19ን መነሻ ለመመርመር ቻይና ገቡ

የዓለም ጤና ድርጅት የጤና ሳይንስ ተመራማሪዎች ቡድን የኮሮናቫይረስን አመጣጥ ለመመርመር የወረርሽኙ መነሻ የተባለችውን የቻይና ማዕከላዊ ከተማ ውሃን ገብተዋል፡፡

ተመራማሪዎቹ የምርመራ ስራቸውን ከማካሄዳቸው በፊት በቻይና የወረርሽኝ ቁጥጥርና እርምጃ አሰራር መሰረት በለይቶ ማቆያ እንደሚቆዩ የቻይና ብሄራዊ የጤና ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በዚህ አስቸጋሪ ወቅት አንድነት እንዲኖር አሳስበው፣ ሁሉም አገራት በኮቪድ-19 መነሻ ላይ ለሚካሄደው ምርምር አዲሱን የኮሮናቫይረስ ዝርያዎች እና ተዛማጅ መረጃዎችን ለተመራማሪዎች እንዲያካፍሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ቻይና ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ ተመራማሪዎች የኮሮናቫይረስ አመጣጥ እና ስርጭት መንገዶች ላይ የሚያካሂዱትን ጥናትና ምርምር እንደምትደግፍ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሻኦ ሊ ጂያን ለሲጂቲኤን ተናግረዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 92 ሚሊየን 848 ሺህ 561 የደረሰ ሲሆን በወረርሽኙ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር 1 ሚሊየን 988 ሺህ 483 ሲሆን፣ 66 ሚሊየን 405 ሺህ 548 ሰዎች ደግሞ ከበሽታው ማገገማቸው የዎርልድ ኦሜትር መረጃ አመልክቷል፡፡