ትግራይ ክልልን ጨምሮ የእለት ደራሽ እርዳታ ለሚሹ ዜጎች ለማድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

መስከረም 13/2014 (ዋልታ) – ትግራይ ክልልን ጨምሮ የእለት ደራሽ እርዳታ ለሚሹ ዜጎች እየተሰራጨ መሆኑን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮምሽኑ በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ 37 የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች እስከ መስከረም 21 ድረስ 182 ሚሊየን ብር እንዲያንቀሳቅሱ ተፈቅዶላቸዋል ብሏል፡፡
ትግራይ ክልል ዕርዳታ ለሚሹ ዜጎች በዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ህብረት እንዲሁም በሲአርሲ በኩል እርዳታ እየደረሳቸው መሆኑን በኮሚሽኑ የህዝብ ግኑኝነትና ኮሙዩንኬሽን ኃላፊው አቶ ደበበ ዘውዴ ተናግረዋል፡፡
ከሰመራ ወደ መቐለ የሚደረገው ጉዞ ሠላማዊ እንዲሆን መደረጉን ተከትሎ 16 ሺሕ 96 ሜትሪክ ቶን የእለት ደራሽ ዕርዳታ የጫኑ 616 ተሽከርካሪዎች እንዲሄዱ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም 5 ሺሕ 825 ሜትሪክ ቶን ምግብ ነክ ያልሆኑ አልባሳት፤ የቤት ቁሳቁስ፤ መድኃኒት ለተረጂዎች እንዲደርስ እየተደረገም ነው ብለዋል፡፡
759 ሺሕ 235 ሊትር ነዳጅ እና 1 ሺሕ 36 ሜትሪክ ቶን ምርጥ ዘር ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባ ተደርጎል ብለዋል ፡፡
በትግራይ የሰብዓዊ እርዳታ ተግባር ለሚያከናውኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት የፋይናንስ ችግር እንዳያጋጥማቸው ለ37 አጋር አካላት እስከ መስከረም 21 ድረስ 182 ሚሊየን ብር እንዲያንቀሳቅሱ መፈቀዱን ተናግረዋል፡፡
ከ500 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች በሚገኙበት የአማራ ክልል 220 ሺሕ ተፈናቃይ ወገኖችን መንግስት እየረዳ ሲሆን፣ 60 ሺሕ የሚሆኑትን ደግሞ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እየረዱ መሆኑን ኢብኮ ዘግቧል፡፡
በአፋር ክልል ከ6 ወረዳዎች ለተፈናቀሉ 76 ሺሕ ዜጎች መንግስት 28 በመቶ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ደግሞ 72 በመቶ እርዳታ እያቀረበ መሆኑም ተገልጿል፡፡