ቻይና በቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ቀዳሚ ሆነች

ቻይና በቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት (FDI) ለመጀመርያ ጊዜ አሜሪካን በመቅደም የምድራችን ቁጥር አንድ አገር ለመሆን መብቃቷን የተመድ ጥናት አመለከተ።

እሑድ ዕለት ይፋ በተደረገው የድርጅቱ ጥናት መሠረት ቻይና አዳዲስ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብ ይሆናል ተብሎ ከተገመተው በአጭር የጊዜ ሂደት አሜሪካን ለመብለጥ ችላለች።

ድርጅቱ ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው ወደ ቻይና ድርጅቶች አዳዲስ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በ4 ከመቶ አድጓል።

በሌላ አነጋገር በፈረንጆቹ 2020 ወደ ቻይና የተመሙ አዳዲስ የቀጥታ ኢንቨስትመንቶች ወደ አሜሪካ ከተመሙት አዳዲስ የቀጥታ ኢንቨስትመንቶች በእጅጉ የላቁ ናቸው።

ይህ የሚያሳየው ቻይና በዓለም ዙርያ ያላት ተጽእኖ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ነው ብሏል ሪፖርቱ።

በአንፃሩ ከውጭ አገራት ወደ አሜሪካ የሚገቡ አዳዲስ የቀጥታ ኢንቨስትመንቶች ባለፈው ዓመት (2020) በግማሽ መቀነሳቸውን ዘገባው አትቷል።

ሆኖም ወደ ቻይና የሚተሙ የቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንቶች ከዕለት ዕለት እየጨመሩ በመምጣታቸው ምክንያት ቻይና ከአሜሪካ ልቃ እንድትገኝ አስችሏታል።

ቻይና ባለፈው ዓመት ብቻ 163 ቢሊዮን ዶላር ወደ አገሯ አዲስ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፈሶላታል።

አሜሪካ ግን 134 ቢሊዮን ብቻ ነው ወደ አገሯ የቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ የቻለችው።

ይህን አሐዛዊ ዘገባ ያወጣው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በንግድና በልማት ኮንፈረንስ (UNCTAD) ላይ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።