አለመግባባትና ግጭትን ለማስቀረት ኢትዮጵያዊያን የጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባ ተገለፀ

መጋቢት 30/2013 (ዋልታ) – ሀገራዊ አንድነትንና ሰላምን ለማስፈን አለመግባባትና ግጭትን ለማስቀረት ኢትዮጵያዊያን የጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባ ተገለጸ።
“ቱባ ወግ ” በተሰኘው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ወርሃዊ የዉይይት መድረክ ላይ የመጋቢት ወር የመወያያ ርዕሱን “የኢትዮጵያውያን የጋራ ጎዳዮች ምንድን ናቸው?” በሚል ጥናታዊ ጽሑፋ ቀርቦ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።
በውይይቱ ኢትዮጵያዊያን ከሚለያዮቸዉና ከሚያጋጯቸው ጉዳዮች ይልቅ አንድ የሚያደርጓቸው የጋራ እሴቶቻቸዉ በርካታ በመሆናቸዉ ሀገራዊ አንድነትንና ሰላምን ለማስፈን የጋራ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንደ መፍትሄ ተነስቷል።
ከጋራ ጉዳዮች ይልቅ ጥቃቅን ልዩነቶች መጉላታቸዉ ምክንያት በመሆኑ የጋራ እሴቶች፣ ባህሎችና ስርዓቶች ላይ ማተኮር ያስፈልጋል ተብሏል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪና ተወካይ አቶ ወርቅነህ አክሊሉ ኢትዮጵያ በአራቱም አቅጣጫ የሚያስተሳስሯቸውና አንድ የሚያደርጓቸዉ በርካታ እሴቶች መኖራቸውን አንስተዉ አባቶቻችን ልዮነቶቻቸዉን ለአንድነታቸው እንደ ምክንያት ወስደው ሃገርን ጠብቀዉ ለእኛ እንዳስረከቡን እኛም ለልጆቻችን ማስረከብ የምንችለዉ የጋራ ጉዳዮቻችን ላይ መግባባት ስንችል በመሆኑ እዚህ ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ብለዋል።
(በህይወት አክሊሉ)