አሜሪካ ምዕራባዊያን አጋሮቿ ኤፍ-16 ተዋጊ ጄት ለዩክሬን እንዲያስታጥቁ ልትፈቅድ መሆኗ ተገለጸ

ኤፍ-16 ተዋጊ ጄት

ግንቦት 12/2015 (ዋልታ) አሜሪካ ምዕራባዊያን አጋሮቿ የራሷ ስሪት የሆነውን ኤፍ-16 ተዋጊ ጄትን ጨምሮ እጅግ ዘመናዊ የጦር አውሮፕላኖች ለዩክሬን እንዲያስታጥቁ ልትፈቅድ መሆኑን ገለጸች።

የአሜሪካ የብሔራዊ ፀጥታ አማካሪ የሆኑት ጃክ ሰሊቫን ፕሬዝዳንት ባይደን ይህንን ውሳኔ ጃፓን ውስጥ እየተካሄደ ባለው የቡድን 7 ስብሰባ ላይ “ለአቻዎቻቸው አሳውቀዋል” ብለዋል።

በተጨማሪም የአሜሪካ ወታደሮች የዩክሬን አቻዎቻቸው የጦር ጄቶቹን አጠቃቀም በተመለከተ ሥልጠና እንደሚሰጡ ገልጸዋል።

ከሩሲያ ጋር ጦርነቱ እየተባባሰ ከሄደበት ጊዜ አንስቶ ምዕራባውያን አጋሮቿ ዘመናዊ የጦር ጄቶችን እንዲያስታጥቋት ስትወተውት የቆየችው የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የአሜሪካን ውሳኔ “ታሪካዊ” ብለውታል።

አሜሪካ ከዚህ ቀደም ለአጋሮቿ ያስታጠቀቻቸው ኤፍ-16 የተባሉትን ዘመናዊ የጦር አውሮፕላኖችን ለሌላ ወገን አሳልፈው መስጠት ከፈለጉ ፈቃዷን መጠየቅ እንዳለባቸው በሕግ ታስገድዳለች።

የአሁኑ የባይደን ውሳኔ ምዕራባዊያን የጦር ጄቶቹን ለዩክሬን ለመስጠት በር የሚከፍትላቸው ከመሆኑም በተጨማሪ ለዩክሬን ሠራዊት ወሳኝ ጥንካሬን የሚሰጥ ነው ተብሏል።

አሜሪካ ከጦር አውሮፕላኖች ውጪ ሌሎች የጦር መሳሪያዎችን ለዩክሬን ስታስታጥቅ የቆየች ሲሆን የጦር ጄቶችን እንደማትሰጥ ፕሬዝዳንት ባይደን ባለፈው የካቲት ገልጸው እንደነበር የቢቢሲ ዘገባ አስታውሷል።