አሜሪካ ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ ምንም የፋይናንስ ድጋፍ ክልከላ እንደማይደረግባት አስታወቀች

ሰኔ 23/2015 (ዋልታ) አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ጥላው የነበረውን የሰብዓዊ መብት ጥስት ክስ በማንሳት ሀገሪቱ ከዚህ በኋላ ምንም አይነት የፋይናንስ ድጋፍና አቅርቦት ክልከላ እንደማይደረግባት አስታወቀች።

የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ ያሳለፈውን “የሰብዓዊ መብት ጥሰት” ፍረጃ ማንሳቱን ለኮንግሬሱ እንዳሳወቀ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሰነድን ጠቅሶ ፎሬይን ፖሊሲ ጋዜጣ ዘግቧል።

የባይደን አስተዳደር ውሳኔውን ለኮንግሬሱ ያሳወቀው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በቅርቡ ባካሄደው ግምገማ፣ ኢትዮጵያ ተከታታይነት ባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ውስጥ እየተሳተፈች እንዳልሆነ ድምዳሜ ላይ ደርሷል በማለት መሆኑን ዘገባው ጠቅሷል።

ውሳኔው አሜሪካ በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ ለኢትዮጵያ መስጠት ያቋረጠቻቸውን ዕርዳታዎች እንደገና እንድትቀጥል በር የሚከፍት እንደነምነ ተነግሯልል።

ለሀገሪቱ ኮንግረስ የተላከው ይህ የውስጥ ማስታወሻ አሜሪካ ይህንን ክስ በማንሳቷ ከዚህ በኋላ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ኢትዮጵያ ከዋሽንግተንም ሆነ ከሌሎች ዓለም አቀፍ አበዳሪዎች ገንዘብ እንዳታገኝ ሲያደርግ የነበረውን መከላከል እንደሚያቆም ያመላክታል።

የአሜሪካ ውሳኔ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) እና ከዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍና ብድር እንድታገኝ የሚያስችል እንደሆነም ተመላክቷል።

ውሳኔው አሜሪካ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት የሻከረውን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማደስ ፍላጎት እንዳላት ያሳያልም ነው የተባለው።