አሜሪካ የቻይና ሰው አልባ ፊኛ መረጃ ሲሰበስብ እንዳልነበር ገለጸች

ሰኔ 23/2015 (ዋልታ) ባለፈው የካቲት ወር በአሜሪካ አየር ክልል ሲያቋርጥ በጀት የተመታውና ንብረትነቱ የቻይና የሆነ ሰው አልባ ፊኛ የስለላ መረጃ እየሰበሰበ እንዳልነበር ፔንታጎን አስታወቀ፡፡

የአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ብርጋዲየር ጀነራል ፓት ራይደር “ባሉኖቹ የስለላ ስራ መስራት እንደሚችሉ እናውቃለን፤ ነገር ግን እስካሁን ባደረግነው ምርመራ የአሜሪካንን ክልል ለማቋረጥ በሞከረበት ወቅት መረጃ አለመሰብሰቡን አረጋግጠናል” ብለዋል፡፡

ሰው አልባ ፊኛው በአሜሪካና በካናዳ የአየር ክልል ውስጥ ለሁለት ሳምንታት ሲንሳፈፍ የነበረ ሲሆን በአሜሪካ ተዋጊ ጀት ተመቶ ስብርባሪው አትላንቲክ ጠረፍ ላይ መውደቁ ይታወሳል፡፡

የቻይና ባለስልጣናት ፊኛው የስለላ እንዳልሆነ ገልጸው የአሜሪካ እርምጃ ከልክ ያለፈ ጥርጣሬ ነው ሲሉ አጣጥለውት እንደነበረም የሚታወስ ነው፡፡

ክስተቱን ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል ውጥረት ነግሶ እንደነበርና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ወደ ቤጅንግ ሊያደርጉት የነበረውን ጉዞ እስከ መሰረዝ ደርሰው እንደነበር ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል፡፡ ሆኖም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዚህ ወር ቻይና መጎብኘታቸው ይታወሳል፡፡