ኢትዮጵያ ወደ ብሪክስ አባልነት

ኢትዮጵያ ወደ ብሪክስ አባልነት
በደረሰ አማረ

ሰኔ 24/2015 (ዋልታ) ዛሬ ላይ ብሪክስ በሚል የምናውቀውና ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካን ያሰባሰበው ህብረት በአውሮፓዊያኑ 2009 በሩሲያ፤ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድና ቻይናን በማሳተፍ የመጀመሪያውን ጉባኤ አካሂዷል፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ በአውሮፓዊያኑ 2010 ደቡብ አፍሪካ ህብረቱን ተቀላቅላለች፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የብሪክስ የመሪዎች ስብሰባ በየዓመቱ ሲካሄድ ቆይቷል። የ2022ቱ የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ በቤጂንግ የተካሄደ ሲሆን የ2023ቱ የመሪዎች ጉባዔ በመጪው ነሐሴ ወር በደቡብ አፍሪካ እንደሚካሄድ ዕቅድ ተይዟል።

የብሪክስ ጥምረት ከዓለም ህዝብ 40 በመቶ በላይ የሚሆነውን ይዟል፡፡ ከዓለም ጠቅላላ ሃብት አንድ አራተኛ የሚሆነውን ድርሻ እነዚህ አምስቱ አገራት ይጋራሉ፡፡ እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ከሆነ ቻይና 70 በመቶ፣ ህንድ 13 በመቶ፣ ሩሲያና ብራዚል 7 በመቶ፣ ደቡብ አፍሪካ 3 በመቶ ኢኮኖሚያዊ ድርሻ በጥምረቱ ውስጥ አላቸው፡፡

ዓለማችን በጥቂቶች ቁጥጥር ስር መዋል የለባትም የሚለው ይህ ህብረት ተጨማሪ መገበያያ ገንዘብ ለዓለም እንደሚያስተዋውቅ መናገሩ አይዘነጋም። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የብሪክስ አባል አገራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የደረሱ ናቸው፡፡ አሁን አሁን በርካታ ታዳጊ አገራትም በዚህ ቡድን ውስጥ ለመቀላቀል ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ አገራት መካከልም ኢትዮጵያ አንዷ ናት።

እንግዲህ ይህንን ግዙፍ ህብረት ለመቀላቀል ኢትዮጵያ በይፋ ጥያቄ ማቅረቧ ታውቋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ጥቅሞቿን ሊያጠናክሩ ከሚችሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር መስራቷን ትቀጥላለች፡፡ ብሪክስ ከኢትዮጵያ ለቀረበለት ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ እንደሚሰጠን እንጠብቃለን ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያም እንደ አፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት መስራች አባል ሀገር እንደመሆኗ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጥቅሟን ለማስከበር ለምታደርገው ጥረት እንደ ብሪክስ ያሉ ጥምረቶችን መቀላቀል አስፈላጊ ነው ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡

ኢራንና አርጀንቲና የብሪክስ አባልነት ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ የኔቶ አባል አገራት ሳይቀሩ ጥያቄ ሲያቀርቡ ተስተውሏል፡፡ ቱርክ፣ ግብፅ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስና አልጄሪያ ተመሳሳይ ህብረቱን የመቀላቀል እቅድ እንዳላቸው ታውቋል፡፡ የፊታችን ነሐሴ በደቡብ አፍሪካ ጉባኤውን እንደሚያደርግ የሚጠበቀው ብሪክስ ህብረቱን ለመቀላቀል ጥያቄ ላቀረቡ አገራት ምላሽ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።

ብሪክስ የአባልነት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ከአገራቱ የህዝብ ቁጥርና ኢኮኖሚያዊ አቅም አንጻር እንደሚመለከት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ወደ 120 ሚሊየን ገደማ መሆኑ፣ በየዓመቱ ወደ 1.5 ቢሊየን ዶላር ገደማ ከቡና የኤክስፖርት ገቢ አቅም መፍጠር የቻለችው ኢትዮጵያ በቆዳና ሌጦ፣ በጨርቃ ጨርቅና በአበባ ምርት ወደ ውጭ በመላክ ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ አቅም እየፈጠረች ያለች አገር መሆኗ የአባልነት ጥያቄዋ አዎንታዊ ምላሽ እንደሚያገኝ ይጠበቃል፡፡ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት እጀግ በፍጥነት እያደጉ ከሚገኙ አምስት አገራት አንዷ ኢትዮጵያ ነች ብሏል፡፡

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ የ2023 ከፊል የሰሃራ አፍሪካ አገራትን አጠቃላይ የምርት እድገት ሲያስቀምጥ ከደቡብ አፍሪካና ናይጄሪያ በመቀጠል ኢትዮጵያ ሦስተኛ ደረጃ መያዟን አመላክቷል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ደቡብ አፍሪካና ናይጄሪያ ካሉ ግዙፍ ኢኮኖሚያዊ አቅም ካላቸው አገራት ተርታ መሰለፏ ከምስራቅ አፍሪካ አገራት በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጧ ሪፖርት ተደርጓል፡፡

ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ፈጣንና ጠንካራ ኢኮኖሚ እየገነባች ያለች ሀገር በመሆኗ የብሪክስ አባልነት ጥያቄዋ አዎንታዊ ምላሽ እንደሚያስገኝላት እየተገለጸ ነው፡፡ ምንም እንኳን ለብሪክስ የአባልነት ጥያቄ ያቀረቡ አገራት ቁጥር ወደ 19 ገደማ እንደሆነ የተነገረ ቢሆንም በአጠቃላይ ድምር የህዝብ ቁጥራቸው 220 ሚሊየን ገደማ የሚሆነው ሦስት አገራት ማለትም ግብጽ፣ ቱርክና ሳውዲ አረቢያ የአባልነት ጥያቄ አቅርበው ምላሽ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ አገራት መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡