አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ እየተሰራ ነው – ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ

የካቲት 25/2013 (ዋልታ) – አምራችና ሸማቹን በቀጥታ የሚያገናኝ የግብይት ስርዓት በመዘርጋት የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ እየተደረገ ያለው ርብርብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።

ምክትል ከንቲባዋ በከተማዋ የተፈጠረውን የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ በተሰሩ ስራዎች ዙሪያ በከተማ ምክር ቤቱ 8ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ ዓመት መደበኛ ጉባኤ ላይ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

የኑሮ ውድነትን ማቃለል የሚችሉ የገበያ ማዕከላትን በማበራከት በአምራቾችና በሸማቾች መካከል ዘመናዊ የችርቻሮ አውታሮችን በማስፋፋት እና የግብይት ሰንሰለትን በማሳጠር  የዋጋ ንረቱን ለመቀነስ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት 720 ሺህ ኩንታል ስኳር ለህብረተሰቡ ለማሰራጨት ታቅዶ 556 ሺህ ኩንታል በላይ ስኳር የተሰራጨ ሲሆን ከ31 ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት ለህብረተሰቡ መሰራጨቱም ተጠቁሟል፡፡

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደጎም የተቋቋመው የሸገር ዳቦ ፋብሪካ በቀን ያመርት የነበረውን 600 ሺህ ዳቦ ወደ አንድ ሚሊየን ከፍ እንዲል ተደርጎ ህብረተሰቡ ጋር ተደራሽ እንዲሆን መደረጉንም ምክትል ከንቲባዋ በሪፖርቱ አመልክተዋል፡፡

የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ የሚያገናኙ ዘመናዊ የገበያ ማዕከላት በከተማዋ መገንባታቸውም ነው የተገለጸው፡፡

የንግድ ስርአቱ ውስጥ የሚስተዋሉ ህገወጥና ኢፍትሃዊ ተግባራትን ለመቆጣጠር 292 ሺህ የሚሆኑ የንግድ ድርጅቶች ላይ  ቁጥጥር እየተደረገ ነው፡፡

ያለ ንግድ ፍቃድ በመነገድ፣ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ፣ በማከማቸት የምርት እጥረት የፈጠሩ የንግድ ተቋማት ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ የእርምት እርምጃ ተወስዷል ብለዋል ምክትል ከንቲባዋ፡፡

በተጨማሪም የከተማዋን ሰላምና ፀጥታ በተመለከተ በተሰራ ስራ 90 ቦንብ፣ 944 ክላሽንኮቭና የተለያዩ ጠመንጃዎች፣ 693 ሽጉጦች በህብረተሰቡ በጥቆማና ብርበራ የተገኙ ሲሆን፣ በተለያየ አግባብ የመዲናዋን ሰላም ለማወክ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 1ሺህ 782  ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል የምርመራ መዝገብ እንዲከፈት መደረጉ ተገልጿል።

(በዙፋን አምባቸው)