አምስተኛው ምዕራፍ የልማታዊ ሴፍትኔት መርሀ-ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ በይፋ ተጀመረ

መጋቢት 20/2013 (ዋልታ) – የአምስተኛው ምዕራፍ የልማታዊ ሴፍትኔት መርሀ-ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ በይፋ መጀመሩን የሚያበስር መርሀ- ግብር እየተከናወነ ይገኛል፡፡
መርሀ ግብሩ በኢትዮጵያ በ1997 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን፣ በወቅቱ 4.5 ሚሊየን የገጠር ነዋሪዎች ተመልምለው የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥላቸው መደረጉ ተጠቁሟል።
5ኛው ምዕራፍ የልማታዊ ሴፍትኔት መርሀ-ግብር እስከ 2025 የሚቆይ ሲሆን፣ በእነዚህ አመታት የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የተለያዩ ድጋፎች ይደረጋል ነው የተባለው።
በመርሀ-ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የግብርና ሚኒስትር ኡመር ሁሴን በሀገራችን በተለይም በገጠሪቱ የሚከሰተውን የምግብ ዋስትና ችግር ለመቅረፍ ባለፉት 15 አመታት ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል ያሉ ሲሆን፣ ባለፉት አራት ምዕራፎች የአደጋ ስጋት ተጋላጭነትን በመቀነስ የስርአተ ምግብ ሁኔታው እንዲሻሻል ተደርጓል ብለዋል።
በ4ቱ ምዕራፎች የገጠር ሴፍትኔት አንድ ወጥ በሆነ መልኩ አለመመራቱና ለመርሀ-ግብሩ ተጠቃሚዎች የሚቀርበው ሀብት እንደ ችግር የተስተዋሉ ናቸው ሲሉም አክለዋል።
በ5ኛው ምዕራፍ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተሳታፊዎችን በማሳደግ ለአንድ አመት ስራዎች ተሰርተዋል ያሉት ሚኒስትሩ፣ የተሻለ አፈፃፀም እንዲኖር ለማስቻል የተጠቃሚ ልየታዎችና ወጥ የሆነ ዘመናዊ አሰራር ለመፍጠር ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።
(በሱራፌል መንግስቴ)