አምባሳደር ታየ አፅቀሥላሴ ማን ናቸው?

አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ በጎንደር ደባርቅ ተወልደው ያደጉና ለሦስት አስርት ዓመታት በዘለቀው የሥራ ዘመናቸው ኢትዮጵያን በተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማት ሆነው አገልግለዋል። በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ኢትዮጵያን በመወከል ይታወቃሉ።

በፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የሰሩና በዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ስትራቴጂክ ጥናት በእንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው ላንካስተር ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡

አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ በተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን ወደ ኒውዮርክ ከማምራታቸው በፊት ለሁለት ዓመታት በግብፅ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል፡፡

አምባሳደር ታየ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እንዲሁም በኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሠርተዋል፡፡

አምባሳደር ታየ በተለያዩ ከፍተኛ ኃላፊነቶች እንዳገለገሉ የሚገለጽ ሲሆን የኢትዮጵያ ህገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሸን ኮሚሽነር ሆነውም ሰርተዋል።

በስቶኮልም፣ በዋሽንግተን፣ በሎሳንጀለስ፣ በኒውዮርክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ረዘም ላለ ጊዜ በዲፕሎማሲው መስክ ኢትዮጵያን አገልግለዋል፡፡

አምባሳደር ታዬ ከጥር 10/2015 ዓ.ም ጀምሮ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ ሚኒስትር ሆነው ተሹመው በመሥራት ላይ እንደነበሩ ይታወቃል።

በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን በ15ኛ መደበኛ ስብሰባ አምባሳደር ታየ የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴን የሥራ ልምድ ዘርዝረው ለምክር ቤቱ ባቀረቡት መሰረት ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ ሹመቱን አጽድቋል፡፡