አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ በሱዳን የቱርክ አምባሳደር ጋር በሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ

አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ

መጋቢት 28/2013 (ዋልታ) – በሱዳን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ በሱዳን የቱርክ አምባሳደር ኢርፋን ናዚር ኦግሉን ጋር በሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱም ሁለቱ አምባሳደሮች በኢትዮጵያና ቱርክ መካከል ያለውን ጠንካራ ወዳጅነትና የኢኮኖሚ ትስስር አድንቀው ተቀራርቦ መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል።

በተጨማሪ አምባሳደር ይበልጣል በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለውን የድንበር ውዝግብ ከዚህ ቀደም በተቋቋሙ የጋራ ኮሚቴዎችና የሕግ ማዕቀፎች መሰረት በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ዝግጁነት ያስረዱ ሲሆን፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድርድር ሂደት ዙሪያም የኢትዮጵያ ፍትሃዊና ምክንያታዊ አቋም በተመለከት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

መንግስት በትግራይ ክልል ለሰብዓዊ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶችና የዓለምአቀፍ ሚዲያ ተቋማት ያልተገደበ ፈቃድ መስጠቱን ጨምሮ ሌሎች ከሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተገናኘ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ተቋማት ጋር የጋራ ምርመራ ለማድረግ ስለተጀመሩ ስራዎችም ገለጻ አድርገዋል።

አምባሳደር ኢርፋን በበኩላቸው፣ ለተደርገላቸው ገለጻ አመስግነው በቀጣይ የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ተቀራርቦ ለመስራት ያላቸውን ዝግጁነት ማረጋገጣቸውን ከሱዳን የኢትዮጵያ ኢምባሲ  የተገኘው መረጃ ያመለክታል።