አርሶ አደሩ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን በኩታ ገጠም በስብጥር እንዲያለማ መደረጉ ምርታማነትን አሳድጓል

ሕዳር 2/2016 (አዲስ ዋልታ)  አርሶ አደሩ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን በኩታ ገጠም በስብጥር እንዲያለማ በመደረጉ ምርታማነትና ተጠቃሚነትን ማሳደጉን በጅማ ግብርና ምርምር ማዕከል የብሔራዊ ቡናና ሻይ ምርምር ፕሮግራም አስታወቀ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ እየተከናወኑ ያሉ የቡና ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ሥራዎች በተለያዩ አካላት ተጎብኝተዋል።

በጅማ ግብርናና ምርምር ማዕከል የብሔራዊ ቡናና ሻይ ምርምር ፕሮግራም አስተባባሪ ለሚ ቤክሲሳ እንዳሉት፣ የምርምር ማዕከላት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሰሩ ነው።

ማዕከላቱ ከቡና ዝርያ ማሻሻል እስከ ምርት አሰባሰብ ቴክኖሎጂን የማለማድ ሥራ እያከናወኑ መሆኑንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በተለይ በምርምር የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በማሰራጨትና ቡናን በኩታ ገጠምና በስብጥር እንዲያለማ በማድረግ ምርታማነቱን ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑናቸውን ገልጸዋል።

ለእዚህም በየዓመቱ ከ300 ኩንታል በላይ የተሻሻሉ ዝርያዎች ቡና አብቃይ ለሆኑ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተሰራጩ መሆኑን ነው አስተባባሪው የጠቀሱት።

“በተለይ ከ44 በላይ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን በማፍለቅ ለሲዳማና ጌዴኦ ስነ-ምህዳር የሚስማሙትን ስድስት ዝርያዎች በአካባቢዎቹ ለማላመድ ተችሏል” ብለዋል።

የፕሮግራም አስተባባሪው እንዳሉት በአካባቢዎቹ በ108 ሄክታር የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን በኩታ ገጠም ከእንሰት፣ ከሙዝ እና ከስራስር ሰብሎች ጋር በስብጥር በማልማት ውጤት ተመዝግቧል።

ለእዚህም በሄክታር በአማካይ ሰባት ኩንታል ብቻ ይገኝ የነበረውን ምርት በሞዴል አርሶ አደሮች ማሳ እስከ 25 ኩንታል ማድረስ መቻሉን ጠቅሰው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ተሞክሮውን የማስፋት ሥራ እየተሰራ መሆኑን የፕሮግራም እተባባሪው ጠቁመዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡናና ቅመማ ቅመም ጽህፈት ቤት የቡናና፣ ቅመማ ቅመም ልማትና ጥበቃ ዘርፍ ሃላፊ አማኑኤል ብሩ በበኩላቸው በክልሉ ከ116 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ቡና እየለማ  ቢሆንም በቡና ተክል እርጅና ምክንያት በሚፈለገው መጠን ምርታማ መሆን አልተቻለም።

ኃላፊው እንዳሉት በክልሉ የቡና ምርታማነት በሄክታር በአማካይ ሰባት ኩንታል ሲሆን ይህም በሞዴል አርሶ አደሮች ከተመዘገበው ውጤት አንጻር ሰፊ ልዩነት አለው።

“ልዩነቱን ለማጥበብ ከምርምር ተቋማት ጋር በመሆን ያረጁ የቡና ተክሎችን በአዲስ የመተካት ሥራ እየተሰራ ነው” ብለዋል።

በተያዘው ዓመት ብቻ ከ9 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ያረጁ ቡናዎችን ነቅሎ በአዲስ የመተካት ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ለዓብነት ጠቅስዋል።

የጌዴኦ ዞን ግብርና መምሪያ ሃላፊ ታጠቅ ዶሪ በበኩላቸው፣ በዞኑ በየዓመቱ ከ10 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የቡና እድሳት ሥራ ይከናወናል።

በዚህም ያረጀ የቡና ተክልን ነቅሎ በአዲስ የመተካት፣ የመጎንደል እንዲሁም ምርታማነት ለማሳደግ የሚረዱ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

በዚህም የቡና ምርታማነትን ማሳደግ እንደተቻለ ጠቅሰው በግብአት አቅርቦት፣ በምርምር እና በእውቀት ሽግግር በኩል የምርምር ማዕከላትና የዩኒቨርሲቲዎች አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን መግለጻቸው ኢዜአ ዘግቧል።