የግንባታ ስራዎችን ከአንድ ማዕከል ሆኖ ክትትል ማድረግ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ይፋ ተደረገ

ሕዳር 2/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በተለያዩ አካባቢዎች የሚከናወኑ የግንባታ ስራዎችን ከአንድ ማዕከል ሆኖ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ የሚያስችለውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ይፋ አድርጓል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የኮርፖሬሽኑ የቦርድ ሰብሳቢ እና የመስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀማድ፣ የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል እና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ይፋ የማድረግ መርሃ-ግብር ተከናውኗል።

ከፕሮጀክቶቹ መካከል በተለያዩ ቦታዎች የሚከናወኑ የግንባታ ስራዎችን ከአንድ ማዕከል ሆኖ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ የሚያስችል ዘመናዊ የዲጅታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሽ ነው።

የኮርፖሬሽኑ የቦርድ ሰብሳቢ ኢንጂነር አይሻ መሀመድ፤ ኮርፖሬሽኑ የለውጥ ሥራዎችን ተግባራዊ በማድረግ የሚታዩ ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

የኮርፖሬሽኑ የቦርድ ሰብሳቢ ኢንጂነር አይሻ መሀመድ

አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶችን በፍጥነት፣ በጥራትና በተያዘላቸው በጀት በማጠናቀቅ በኩል ተወዳዳሪ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኮርፖሬሽኑ አሁን ላይ ከ55 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው 67 ፕሮጀክቶችን በላቀ ብቃት እየገነባ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በተለያዩ አካባቢዎች የሚከናወኑ የግንባታ ስራዎችን ከአንድ ማዕከል ሆኖ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ የሚያስችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ይፋ ማድረጉንም አድንቀዋል።

የዲጂታል ሥርዓቱ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ፣ በሚፈለገው ጥራትና ፍጥነት እንዲከናወኑ ለማስቻል የላቀ አበርክቶ የሚኖረው መሆኑንም ጠቁመዋል።

“የግንባታ ዘርፉ ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ጥገኛ መሆኑ በሥራዎች ውጤታማነት ላይ ጫና ፈጥሯል” ያሉት ኢንጂነር አይሻ ኮርፖሬሽኑ መሰል ችግሮችን የሚፈታ የግንባታ ግብዓት ማምረቻና ማከፋፈያ ወደ ሥራ ማስገባቱንም አድንቀዋል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው፤ ኮርፖሬሽኑ በግንባታ ግብዓት አቅርቦት ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለማቃለል እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።