አቶ አገኘሁ ተሻገር በጎንደር ከተማና አካባቢው በ7 ቢሊየን ብር ወጭ በግንባታ ላይ ያሉ መሰረተ ልማቶችን ጎበኙ

ግንቦት 25/2013 (ዋልታ) – የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በጎንደር ከተማና አካባቢው በ7 ቢሊየን ብር ወጭ እየተገነቡ የሚገኙ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ጎብኝተዋል፡፡

ከተጎበኙ መሰረተ ልማቶቹ መካከል በ5 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ወጭ እየተገነባ የሚገኘው የመገጭ የመጠጥ ውሃና መስኖ ግድብ ፕሮጀክት አንዱ ነው።

በተጨማሪም በ860 ሚሊየን ብር ወጭ እየተገነባ የሚገኘው ከአዘዞ መሰረት ትምህርት ቤት ያለው የ10 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ኮንክሪት አስፓልት መንገድ ስራ በርዕሰ መስተዳድሩ ተጎብኝተዋል።

እንዲሁም በጎንደር ከተማ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት የሚሰጠው የአንገረብ ግድብን የደለል መሞላት ችግር ለማቃለል በ100 ሚሊየን ብር ወጭ የተጀመረው የማጣሪያ ስራም የጉብኝቱ አካል ነው።

ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ አገኘሁ ተሻገር በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት፣ የመገጭ መስኖና የመጠጥ ውሃ ግድብ ፕሮጀክትን በመጭው ዓመት አጋማሽ ለማጠናቀቅ መንስግት አቅጣጫ አስቀምጦ እየተሰራ ነው።

በጉብኝቱ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችን ጨምሮ የከተማው ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላትና የከተማው ታዋቂ ግለሰቦችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።