አቶ ደመቀ ለተመድ የጸጥታው ምክር ቤት አምባሳደሮች በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ገለፃ አደረጉ

አቶ ደመቀ መኮንን

የካቲት 26/2013 (ዋልታ) – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አምባሳደሮች እና ተወካዮች በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ገለፃ አድርገዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መንግስት በትግራይ ክልል ያሉትን የሰብአዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ጥረቱን አጠናክሮ እንደቀጠለና ይህም የህግ ማስከበር እርምጃው ስኬታማ መደምደሚያ ላይ በመድረሱ የተገኘው ከፍተኛ ውጤት ነው ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በክላስተር ላይ በተመሠረተ አቀራረብ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ የሰብአዊ ዕርዳታ ማድረስ መቻሉን የገለጹት አቶ ደመቀ፣ በህወሃት ኃይሎች የወደሙ መሰረተ ልማቶች በመገንባት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

እስካሁን ድረስ በክልሉ የሚታየውን የሰብአዊ ፍላጎት ለማሟላት መንግስት 40 ቢሊየን ብር በማውጣት 70 በመቶውን የሸፈነ ሲሆን፣ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተገኘው 30 በመቶው ብቻ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ጋዜጠኞች በአሁኑ ወቅት በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ ጉዳዮችን የመዘገብ መብት የተሰጣቸው ሲሆን፣ ባለፉት ቀናትም የታሰሩት መለቀቃቸውን አቶ ደመቀ አስታውቀዋል፡፡

አክለውም መንግስት ችግሮችንና ሌሎች እንቅፋቶችን ለመፍታት ያለመታከት እንደሚሰራ ሁሉ ጋዜጠኞች እና የሰብአዊ ሰራተኞችም የሙያ ስነምግባራቸውን በማክበር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

ሰላማዊ አጋርነትን ማጎልበት በዓለም አቀፍ ህግ መርሆዎች የሚመራ የኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ ተልዕኮ መሆኑን ገልፀው፣ ኢትዮጵያ አንድም የውጭ ሀገር ወታደር በምድሯ ውስጥ እንዲቆይ በጭራሽ እንደማትፈቅድ ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ለሚያደርጉት ድጋፍ ለሁሉም አጋር አካላት ያላቸውን አድናቆት በመግለጽ፣ አጋርነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡