አቶ ደመቀ መኮንን ከተሰናባቹ የአፍሪካ ህብረት ምክትል ኮሚሽነር ጋር ተወያዩ

የካቲት 25/2013 (ዋልታ) – የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተሰናባቹ የአፍሪካ ህብረት ምክትል ኮሚሽነር አምባሳደር ክዌሲ ኳሪቴይ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ምክትል ኮሚሽነሩ በኢትዮጵያ የጋና አምባሳደር በነበሩበት ወቅት እንዲሁም በህብረቱ ምክትል ኮሚሽነርነታቸው ለሰጡት አገልግሎት ምስጋና አቅርበው፣ በጋና እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው መልካም ግንኙነት መጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በትግራይ ክልል እየተደረገ ያለውን የሰብአዊ ድጋፍ አስመልክተው ማብራሪያ የሰጡት አቶ ደመቀ፣ በህግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት የአፍሪካ ህብረት ጉዳዩን በመረዳት ለወሰደው አቋም አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

ምክትል ኮሚሽነር አምባሳደር ክዌሲ ኳሪቴይ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ በነበራቸው የቆይታ ጊዜ ስለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው፤ ከኢትዮጵያውያን ጋር ያላቸውን ወዳጅነት እንደሚቀጥሉ መግለፃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡