ዲፕሎማቶች በዳያስፖራ ዲፕሎማሲ ላይ የማስተባበር ተልዕኳቸውን እንዲወጡ ተጠየቁ

የካቲት 25 /2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ አገሩን እንዲያለማ ለማስቻል በየሚሲዮኖች የሚመደቡ ዲፕሎማቶች በዳያስፖራ ዲፕሎማሲ ላይ ልዩ የማስተባበር ተልዕኮ እንዲወጡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጠየቀ።

የሚኒስቴሩ ተጠሪ ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ በተለያዩ አገሮች ሚሲዮኖች ለተመደቡ አዳዲስ የዳያስፖራ ክላስተር አስተባባሪዎችና ዲፕሎማቶች የሁለት ቀናት ስልጠና እየሰጠ ነው።

ስልጠናውን በይፋ የከፈቱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ኤጀንሲው በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች ቅርንጫፎቹ ውጤታማ ስራዎችን እያከናወነ ስለመሆኑ አንስተዋል።

በዳያስፖራና በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ይበልጥ ውጤታማ ስራዎችን ለማከናወን ኢትዮጵያዊያን በሚበዙባቸው አገሮች ሚሲዮኖች፣ አስተባባሪዎችና ዲፕሎማቶችን አሰልጥኖ መመደብ ተገቢ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተለይም የዳያስፖራ ማኅበረሰቡን አስተባብሮ ለአገሩ ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንዲያደርግ ማድረግ ወቅቱ የሚፈልገው ትልቅ ተልዕኮ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ዳያስፖራው ጠበቃ፣ ዳኛና ወታደር ሆኖ እንዲሰለፍ፣ በልማት እንዲሳተፍ፣ ራሱንና አገሩን እንዲለውጥ የማስተባበር ሃላፊነት ለምድብተኛ ዲፕሎማቶች ልዩ ተልዕኮ በመሆኑ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ ዲፕሎማቶች በተመደቡበት አገርና አህጉር ብቻ ሳይሆን ከሌሎች አገራትና አህጉራት ሚሲዮን ዳያስፖራ አስተባባሪዎች ጋር በመቀናጀት ለዜጋ ዲፕሎማሲ ድልድይነት የ24 ሠዓት ስራ ይጠብቃቸዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው፣ የዳያስፖራ ዲፕሎማሲ ውጤት እያስገኘ መሆኑን አስታውሰዋል።

ጅምሩን በተሻለ መንገድ ለመፈጸም በእውቀት ትጥቅ መያዝ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ስልጠናው የተልዕኳቸውን መሳካት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

የዳያስፖራው ተሳትፎ እንዲጎለብት ከዲፕሎማቶች ብርቱ ስራ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።