ደቡብ ሱዳን በናይል የተፋሰስ ማዕቀፍ ስምምነት ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ ጥናት እያካሄደች መሆኑ ተገለፀ

የካቲት 25 /2013 (ዋልታ) – ደቡብ ሱዳን በናይል የተፋሰስ ማዕቀፍ ስምምነት ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ ጥናት እያካሄደች መሆኗ ተገለጸ።

የደቡብ ሱዳን መንግስት ሰነዱን ለማፅደቅ ከመስማማቱ በፊት ለአገሪቱ ያለውን አንድምታና ጠቀሜታ ለመረዳት በማእቀፍ ስምምነቱ ላይ ጥናት እያካሄደች መሆኑን መቀመጫውን ደቡብ ሱዳን ያደረገው የዐይን ራዲዮ አስነበበ።

ለጥናቱ መነሻም አገሪቱ ከአባይ ውሃ ድርሻ ላይ ተጠቃሚ እንድትሆን ስምምነቱን እንድታጸድቅ ኢትዮጵያዊ ዲፕሎማት ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ እንደሆነ ተገልጿል።

በጁባ የኢፌዴሪ ኤምባሲ ምክትል ሚስዮን መሪ አምባሳደር ዘላለም ብርሃን፤ ስምምነቱ የሚያጋጥሙ ችግሮች በማስወገድ እና የደቡብ ሱዳንን ምጣኔ ሃብት እንዲዳብር ለማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ስለመናገራቸው ጣቢያው አስነብቧል።

ስምምነቱ በተፋሰሱ አገሮች መካከል ወንዙን በትብብር በማልማት፣ የሚገኙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ለመጋራት እና በቀጠናው ሰላምና ፀጥታ ዙሪያ መስራት የሚያስችል መሆኑ በዘገባው ተጠቅሷል።

የአባይን ወንዝ ተፋሰስ አጠቃቀም፣ ልማት፣ ጥበቃ፣ አያያዝ እና አስተዳደር በሚመለከት በተፋሰሱ አገሮች መካከል ትብብር ለማድረግ ተቋማዊ አሰራር እንደሚፈጥርም ተጠቁሟል።

ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ እና ቡሩንዲ ስምምነቱን የፈረሙ ሲሆን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ደግሞ ትፈርማለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ተመላክቷል።

የደቡብ ሱዳን ውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ምክትል ሚኒስትር ዴንግ ዳው ዴንግ ከዐይን ራዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ እንዳሉት፤ ስምምነቱ ቀጣይ የሚደራጀውን ብሔራዊ የፓርላማ አባላት ውይይትን ይጠብቃል።

ምክትል ሚኒስትሩ የስምምነት ማእቀፉን ጥናት ከተጠናቀቀ በኋላ አገራቸው በመረጃ ላይ ተመስርታ እንደምታጸድቀው አስረድተዋል።

ግብፅ የናይል ወንዝን ፍሰት እ.አ.አ. በ1929 በእንግሊዝ የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነት ላይ በመመስረት ተቆጣጥራ መቆየቷን ጠቁመዋል።

የተፋሰሱ አገሮች “እንደ መስኖና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችን ከአባይን ውሃ ላይ ለመጠቀም ከግብፅ ፈቃድ መጠየቅ ሰልችቷቸዋል” ብለዋል፡፡

ደቡብ ሱዳን የተሻሻለውን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ አሁንም ስራ ላይ መሆኗን ዐይን ራዲዮን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል፡፡