አንቶኒ ብሊንከን ከቻይናው አቻቸው ጋር ‘ግልጽነት የተሞላበት’ ንግግር ማድረጋቸው ተጠቆመ

ሰኔ 12/2015 (ዋልታ) አንቶኒ ብሊንከን ከቻይናው አቻቸው ጋር ‘ግልጽነት የተሞላበት’ ንግግር ማድረጋቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።

አንቶኒ ብሊንከን ከቻይናው አቻቸው ጋር በነበራቸው ውይይት ዲፕሎማሲዊ ግንኙነትን ስለማስቀጠል እና የግንኙነት መስመሮች ከፍት መሆን እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አመላክቷል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከቻይና ባለስልጣናት ጋር ለሁለት ቀናት የሚዘልቅ ንግግር ለማድረግ ትናንት ቤጂንግ መግባታቸው የሚታወስ ሲሆን ጉዟቸውም የአሜሪካ ዲፕሎማት ወደ ቻይና ሲጓዝ ከአምስት ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያው ያደርገዋል ተብሏል።

ብሊንከን ይህን ጉዞ ለማድረግ አቅደው የነበረው ከአምስት ወራት በፊት የነበረ ቢሆንም ሰላይ ነች የተባሉ ግዙፉ የቻይና ፊኛዎች አሜሪካ ሰማይ ላይ ከታየች በኋላ ጉዟቸውን መሰረዛቸው ይታወሳል።

የአሜሪካ ባለስልጣናት ከብሊንከን ጉዞ በፊት ዋነኛው የብሊንከን የጉዞ ዓላማ እጅግ ውጥረት ያየለበትን የአሜሪካ-ቻይና ግንኙነት ማረጋጋት እንደነበር መግለፃቸውን የቢቢሲ ዘገባ አስታውሷል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኪን ጋንግ አገራቸው ከአሜሪካ ጋር የተረጋጋ እና ገንቢ የሆነ ግንኙነት ለመፍጠር ፍላጎት አላት ብለው መናገራቸውም ተዘግቧል፡፡

ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ውይይት ካደረጉ በኋላ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለጉብኝት ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ለመምጣት መስማማታቸውም ተጠቁሟል።