ከተለመደው ክስ ጀርባ የሚታይ የድል ጮራ!

ከተለመደው ክስ ጀርባ የሚታይ የድል ጮራ!
በሳሙኤል ሙሉጌታ

ሰኔ 12/2015 (ዋልታ) ሀቀኛ ዳኛ በማይገኝበት ወና ፍርድ ቤት ውስጥና የሰናፍጭ ታክል እውነት በማይሞላ ክስ ላይ ተመስርተው ኢትዮጵያን መወንጀል ፋሽን ያደረጉት ምዕራባዊያን እነሆ ዘንድሮም በሌላ የሐሰት ትርክት ብቅ ብለዋል፡፡

የስንዴ አምራችና ላኪዋን ሀገር፤ ስንዴያችን የት ሄደ ብለው የአዞ እምባቸውን እያፈሰሱባት ይገኛሉ፡፡ ትናንት ኢትዮጵያ እርዳታው ለተገቢው አካል እየደረሰ አይደለም ብላ አቤቱታዋን ስታሰማ ጆሮ ዳባ ያሉት እነዚሁ ወጣ ገባ ወዳጅ ሀገራት ዛሬ ተመልሰው ራሷኑ መጠየቅ ጀምረዋል፡፡ ኢትዮጵያ አይደለም እርዳታ ከሚያስፈልገው ከራሷ ህዝብ ልትቀንስ ይቅርና ሀገራት የህልውና ችግር ሲገጥማቸው እንኳ ነፍሳቸውን እንዲሰጡ ዜጎቿን እስከ ሩቅ ምስራቅ ሀገር የምትልክ ቸር ሀገር ናት፡፡

ታዲያ ምዕራባዊያን ምን ይሁን ሲሉ እንደዚህ አይነት ክስ መዘዙ የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አይቀሬ ነው። መልሱ አጭር ነው። ከራሷም አልፎ ቀጣናውን መቀየር የሚችለው የድል ግስጋሴዋ ለምዕራባዊያን ትልቅ ስጋት ፈጥሯል፡፡ ይህም ደግሞ እነሱ ለዘመናት እየተከተሉት በመጡት የካሮትና ዱላ ፖሊሲያቸው ላይ ትልቅ አብዮትን ሊፈጥር እንደሚችል በመታመኑ ነው፡፡

ካሮቱን ስሰጥህ ዳቦ ነው ብላ
አሻፈረኝ ካልክ አድርጌው ዱላ…. እንዳለው ዘፋኙ የካሮትና ዱላ ፖሊሲ በምዕራባዊያን ዘንድ እጅግ ተግባራዊ እየሆነ የሚገኝ የዘመናዊ ቅኝ አገዛዝ ስልት ነው፡፡ ካሮቱ በተመሳሳይ ሰዓት እርዳታም ማስፈራሪያም መሆን የሚችል አስማት ቀመስ እሳቤ ነው፡፡ ሲልኩህ ወዴት ፤ ሲጠሩህ አቤት ብለህ ወዲህ ወዲያ የምትል ጭራ ከሆንክ ካሮቱ በአይነት በአይነቱ ሊቀርብልህ ይችላል፡፡ እሱም ይችላል ነው፡፡ በነገራችን ላይ አንድ መታወቅ ያለበት እውነት ቢኖር የምዕራባዊያን አብዛኛው እርዳታ ‘ሀብታሞች ደሃን ተጠቅመው የበለጠ ሀብታም የሚሆኑበት’ ስትራቴጂ እንጂ እውን ከልብ ዕዝነት የመነጨ መስጠት አይደለም፡፡ ብቻ ካቴና አልባ ባርያ መሆንን የመረጠ መሪና ሀገር ሉዓላዊነቱን ሽጦ ሞልቶ የማይሞላ እርዳታን ማስገባት ይችላል፡፡

በተቃራኒው ደግሞ ካሮቱ ይቀርና የዱላው እሳቤ በራስ መርህ ከመጓዝና ልማትን ከማፋጠን ይመነጫል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ተጠቃሽ ሀገር ነች፡፡ ከጥንትም ጭራን ሳይሆን ጥርስን መሆን የምትመርጠው ሀገረ ኢትዮጵያ ከካሮቱ ክብሯን የምታስቀድም ኩሩ ሀገር ነች፡፡ በሉዓላዊነቷ ድርድር የማታውቅ! በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አሳውን መቀበል ብቻ ሳይሆን የአሳ ማጥመድ ብልሃቱን ያወቀችበት ኢትዮጵያ መረቧን መጣል ከጀመረች ሰነባብታለች። ይህ እንቅስቃሴም ታዲያ ለብዙዎች ምቾትን ነስቶ ቆይቷል። በእርግጥ እንደፈሩትም አልቀረ፤ ሀገሪቱ በየዓመቱ ለስንዴ ግዥ ታወጣ የነበረውን ከ710 ሚሊዮን ዶላር በላይ አስቀረች፡፡ ስንዴያችሁ ወደብ ደርሷል፤ ኑና ውሰዱ የማትባል ሀገር ሆና አረፈችው። ከውጭ የምታስገባውን ስንዴ ትታ ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ምርቷ መሸፈን ቻለች። ይባስ ብሎም ምርቷ ከሀገር ውስጥ ፍጆታዋ ተርፎ ለጎረቤት ሀገራት እስከ መላክ የደረሰ ለውጥን አስመዘገበች። “ከእባካችሁ ስጡኝ” ወደ “እባካችሁ እንኩ” ተሸጋገረች፡፡ በእርግጥ ሀገሪቱ አሁንም ቢሆን እርዳታ አያስፈልጋትም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ከፍትፍቱ ፊቱ እንዲሉ መስጠቱ የሀገር ክብርንናና ሉዓላዊነትን መንካት የለበትም የሚለው መርህ መሪዋ እና ህዝቧ ያስቀመጡት ቀይ መስመር ነው፡፡

ታዲያ ይህ የካሮትና ዱላ እሳቤ ኢትዮጵያ ላይ የሚሰራ አልመስል ያላቸው ሀገራት አሁን ወደ ተለመደ የክስ ጨዋታቸው ተመልሰዋል፡፡ ስንዴ ጠፍቶናል አሉ፡፡ ስንዴ አምራቿን ሀገር ስንዴያችንን አይተሻል ወይ ሲሉ ጠየቁ፡፡ ይህ ለሰሚውም ቀልድ ይመስላል፡፡

በእርግጥ ምዕራባዊያን ኢትዮጵያን የከሰሱበት ጉዳይ የስንዴ እንዳልሆነ ራሳቸውም ያውቁታል። ክሱ ሌላ ገፅታ አለው። በምዕራባዊያን ዘንድ በሁለት እግር ለመቆም የሚደረግ መንገዳገድ እንደ ወንጀል ስለሆነ ከሰሱን። በምዕራባዊያን ዘንድ አልታዘዝም የራሴ መርህና እሳቤ አለኝ ማለት ክስ ያስመሰርታል። በምዕራባዊያን ዘንድ መቀበል እንጂ የሚቻለው አምራችነት ትልቅ ጥፋት ስለሆነ በየሚዲያዎቻቸው የድርሰት ክስ ማስነበብ ጀመሩ። ታዲያ ከእነዚህ ከተለመደው የምዕራባዊያን ክስና ወንጀል ጀርባ ፍንትው ብለው የሚታይ የድል ጮራ አለ። የያዝነው መንገድ ልክ ነው ማለት ነው። ራስን ብሎም ቀጣናውን የመቀየር እንቅስቃሴ። የሚሰሩ እንጂ የሚለምኑ እጆችን ማስቀረት። በብልፅግና መንገድ መጓዝ። የአምራችነት መንፈስ መፍጠር። እነዚህ የድል ጠረን ናቸው ለምዕራባዊያን ክስ መነሻ የሆኑት። እንጂ እውነቱማ የአደባባይ ሚስጥር ነው።

ሰላም፣ እድገት፣ ብልፅግና ለአህጉሪቱ!