አንድነታችንንና ፍጹም ሙሉነታችንን ለዓለም ሕዝብ እናሳይ – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ሰኔ 05/2013(ዋልታ) – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “የክብ ባህላችን” በሚል ባህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ፅሁፍ “በእኩልነትና በመያያዝ አንድነታችንንና ፍጹም ሙሉነታችንን ለዓለም ሕዝብ እናሳይ” ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

“ቤታችን፣ ምጣዳችን፣ ድስታችን፣ ሌማት ገበታችን፣ እንጀራ ዳቧችን፣ስኒ ጀበናችን ሁሉ ክብ ነው። በክብ እንኖራለን፤ ከብበን እንበላለን። ከብበን እንዘፍናለን፤ ከብበን እናለቅሳለን።” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክብ ውስጥ ሁሉም እኩል መቀመጫ እኩል ድርሻ አለው ብለዋል።

ክብ የሙሉነት፣ የፍጽምና፣ የወሰን የለሽነት፣ የዘላለማዊነትና የእኩልነት ተምሳሌት መሆኑን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንጀራ ቆራርጠን ለየብቻ መብላት ከመጀመራችን በፊት በትልቁ ባላአንበሳ ትሪ ወይንም ሌማት ላይ ተዘርግቶ፣ ወጡ ከመሐል ላይ ወጥቶ፣ ሁሉም በጋራ ይቋደስ ነበር ብለዋል። “በክብ ጥቅልል ጉርሻ ፍቅራችንን መጋራት የተለመደ ነው።

ከእንስራና ጋኑ እየተቀዳ ጠላና ብርዙ ሁሉም ከቀንድና ከቅል በተሠሩ ክብ መጠጫዎች በጋራ ይጎነጭ ነበር።”

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ዛሬም ኢትዮጵያን እንክበብ፤ አንድነትና ሙሉነታችንን፣ መያያዝ መፋቀራችንን ሊከፋፍሉና ሊሸራርፉ የሚገዳደሩንን እንድናሸንፍ ማንንም ጣልቃ የማያስገባ ክብ እንፍጠር ብለዋል።