የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ከቻይና ህዝቦች የወዳጅ ሀገራት አሶሴሽን ፕሬዚዳንት ሚስተር ያንግ ዋንሚንግን ጋር ተወያዩ

መጋቢት 11/2016 (አዲስ ዋልታ) የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ የቻይና ህዝቦች የወዳጅ ሀገራት አሶሴሽን ፕሬዚዳንት የሆኑትን ሚስተር ያንግ ዋንሚንግን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይቱ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ የሁለቱ ሀገራት ጠንካራ ታሪካዊ ግንኙነት በመንግስት ለመንግስት ደረጃም ሆነ በፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጎለብት ብልፅግና ፓርቲ አበክሮ እንደሚሰራ ገልፀዋል።

በሁሉም መስኮች ኢትዮጵያ እና ቻይና የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸውና ዘመናትን የተሻገረው የሁለቱ ሀገራት መርህ ለበስ ግንኙነት ወደ ተሻለ ትብብር እና የጋራ ተጠቃሚነት እንዲሻገር ብልፅግና ፓርቲ ፍላጎት እንዳለው አንስተዋል።

ሁለቱ ሀገራት በጋራ ጉዳዮች ላይ በመተባበር በዘላቂነት ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማስመዝገብ እየጣሩ እንደሚገኙና በርካታ የቻይና ኢንቬስተሮችም በኢትዮጵያ መዋእለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ እንደሚገኙም አብራርተዋል።

በመሰረተ ልማት፣ በትምህርት፣ በስልጠና እና በልምድ ልውውጥ ከቻይና መንግስት ለተደረጉ ድጋፎች ምስጋናቸውን አቅርበው በቀጣይም በፓርቲ እና በመንግስት ደረጃ ላይ ያሉ ግንኙነቶችን ወደ ህዝብ ለህዝብ ለማሻገር ጅምር ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ለዚህም የከተሞች እህትማማችነት ስምምነቶች፣ የዩኒቨርሲቲዎች ትብብር፣ የባህል ልውውጥ፣ የተማሪዎች የተግባራዊ እውቀት ልውውጥ እና የወጣቶች ልማት አስፈላጊዎች መሆናቸውንና ጠንካራ ስራ ሊሰራባቸው እንደሚገባ አውስተዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት መካከል ከቀዳሚዎቹ እንደሆነች እና በዚህም መነሻነት የብሪክስ ሀገራትን ጥምረት እስከ መቀላቀል ያደረሰ ውጤት እንዳገኘችም ምክትል ፕሬዝዳንቱ አንስተዋል።

በተለይም በእርሻ፣ በታዳሽ ሀይል አቅርቦት፣ በማኒዩፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪና በቱሪዝም ዘርፍ ሀገራችን ኢትዮጵያ በርካታ ውጤቶችን እያስመዘገበች እንደምትገኝ በቀጣይም ከወዳጅ ሀገራት ኢንቬስተሮች ጋር መልማት የሚችሉና ዘርፈ ብዙ ውጤት ሊያስገኙ የሚችሉ ሰፋፊ የኢንቨስትመንት እድሎች እንዳሉም ጠቅሰዋል።

የቻይና ህዝቦች የወዳጅ ሀገራት አሶሴሽን ፕሬዚዳንት ሚስተር ያንግ ዋንሚንግ በበኩላቸው ብልፅግና ፓርቲ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ በከተማ ልማት እና በማህበራዊ መስኮች ያገኛቸው ድሎች በርካታ መሆናቸውን ገልፀው ለተመዘገበው ስኬት ያላቸውን አክብሮት ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ብቻም ሳይሆን ለቀጠናው እና ለመላው አፍሪካ ትልቅ መነሻ ነጥብ መሆኗን በማንሳት በተለያዩ መስኮች ያሉ ግንኙነቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉና የብሪክስ ሀገራት ጥምረት አባል መሆኗም ተጨማሪ የትብብር መስኮችን የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

በህዝብ ለህዝብ ደረጃ ግንኙነቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል ቻይና ፍላጎት እንዳላት እና ለዚህም ማስፈፀሚያ ይሆን ዘንድ ከዘጠኝ የኢትዮጵያ ከተሞች ጋር ያለውን የከተሞች ለከተሞች ግንኙነታቸው ይበልጥ ለማዳበርና አዳዲስ ከተሞች ጋርም ግንኙነት ለመመስረት ብርቱ ፍላጎቶች እንዳሉ ነው ያነሱት።

ኢትዮጵያ ለቻይና ስትራቴጂክ አጋር እንደሆነችና በቀጣይም በሁሉም መስኮች ትብብርን በማጠናከር የሁለቱ ሀገራት የህዝቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቻይና መንግስት በኩል በትኩረት እንደሚሰራ ቃል መግባታቸውን ከፓርቲው ማህበራዊ ትሥሥር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡