አየር ኃይል ራሱን እያደራጀና እያዘመነ እንደሚገኝ ተገለጸ

ግንቦት 15/2014 (ዋልታ) አየር ኃይል በአደረጃጀት፣ በትጥቅ፣ በስልጠና እና በሰው ኃይል ግንባታ ራሱን እያደራጀ እና እያዘመነ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በኢፌዴሪ አየር ኃይል የማዕከላዊ አየር ምድብ በግዳጅ አፈፃፀማቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የሰራዊቱ አመራርና አባላት የዕውቅናና የማበረታቻ ሽልማት መርኃ ግብር አካሂዷል።

የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ አየር ኃይሉ “ሠራዊት ሀገር እንጂ ብሔር የለውም” ከሚለው የአስተሳሰብ ለውጥ ጀምሮ በአደረጃጀት በትጥቅና ስልጠና እንዲሁም በሰው ኃይል ግንባታ እራሱን እያደራጀና እያዘመነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

አሸባሪው ትሕነግ  በሰሜን ዕዝና ሰሜን አየር ምድብ ላይ የፈፀመውን አረመኔያዊ ጥቃት ተከትሎ በተወሰዱት ተከታታይ ዘመቻዎች የአየር ምድቡ ጀግኖች መስዋዕትነትም ጭምር በመክፈል አኩሪ ታሪክ ሰርተዋል ብለዋል።

ዋና አዛዡ በቀጣይም ለሚጠብቀን ማንኛውም ግዳጅ እራሳችንን ይበልጥ በማዘጋጀት ለኢትዮጵያ የሚመጥን ታላቅ አየር ኃይል የመገንባት ጉዟችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት።

የማዕከላዊ አየር ምድብ አዛዥ ኮሎኔል ወንዱ ኬዳ በበኩላቸው አየር ምድቡ ከተቋማዊ ሪፎርሙ ወዲህ በስልጠናና በጥገናው ዘርፍ ብሎም ዝግጁነትን በማረጋገጥ ረገድ ስኬቶችን በማስመዝገብ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው በአየር ምድቡ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎችና ምቹ የሥራ ቦታን የመፍጠር ጅምሮችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

እውቅናና የማበረታቻ ሽልማት የተሰጣቸው የሰራዊት አባላት ዕውቅናና ሽልማቱ የበለጠ የሥራ ተነሳሽነትን የሚፈጥርላቸው መሆኑን ገልፀው ወደ ፊትም የሚሰጠንን ማንኛውም ግዳጅ ለመወጣት ዝግጁ ነን ማለታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።