ኢትዮጵያና ጂቡቲ የባህር-አየር ካርጎ አገልግሎት ለመጀመር ተስማሙ

የኢትዮጵያ አየር መንገድና የጂቡቲ የነፃ ቀጠናና ወደብ ባለስልጣን በጋራ የባህር-አየር ካርጎ አገልግሎት ለመጀመርና የአህጉሪቱን ንግድ ይበልጥ ለማሳለጥ በሚቻልበት ዙሪያ ለመስራት ተስማሙ።

ስምምነቱ ከቻይና ወደ አፍሪካ የሚሻገረው ከ400 ሺህ ቶን በላይ ምርትና ሸቀጥን በባህር-አየር በማያያዝ ከጂቡቲ ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ፈጣን የካርጎ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ተብሏል።

የባህር-አየር ካርጎ አገልግሎቱ ውጤታም ከሆነ የአየር መንገዱን የካርጎ አገልግሎት በእጥፍ ሊያሳድግ እንደሚችልም ተጠቁሟል፡፡

በውይይቱ በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ፣ የጂቡቲ ነፃ ቀጠናና ወደብ ባለስልጣን ሊቀመንበር አቡበከር ኡመር ሃዲ፣ የኢትዮጵያ እና የጂቡቲ አየር መንገድ ተወካዮች፣ የቻይና መርቻንት ሃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ መሆናቸውን ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።