ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራዊያን በእንግሊዝ የድጋፍ ሰልፍ አካሄዱ

መኖሪያቸውን በእንግሊዝ ያደረጉ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን የድጋፍ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡
በእንግሊዝ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ መላላትን ተከትሎ በለንደንና በስኮትላንድ በተካሄዱ የድጋፍ ሰልፍ በጠላቶች ድብቅ ሴራ ምክንያት የብሔር ተኮር ጥቃት ሰለባ የሆኑ ወገኖችን ዘክረዋል፡፡
የብሔር ተኮር ጥቃትን መንግሥት እንዲያስቆምና ጥፋተኞችን ለፍርድ እንዲቀርብ ጠይቀዋል፡፡ ሕዝብም ያለውን ሴራ ተገንዝቦ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡
የሰልፉ አስተባባሪዎች እንደገለፁት አንዳንድ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት እና መንግሥታት እንዲሁም አንዳንድ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በተለይም በትግራይ ክልል ከተካሄደው የሕግ ማስከበር እርምጃ ጋር ተያይዞ በተዛቡ መረጃዎች መነሻነት በኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ እንዲሁም በኤርትራ መንግስት ላይ እያደረጉት ያለውን አሉታዊ ዘመቻ በጽኑ አውግዘዋል፡፡
ሰልፈኞቹ መንግሥት እየወሰደ ያለውን የሕግ ማስከበር ሂደት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡ በውጭ ያሉ የጁንታው ቡድን አባላት ባለፉት ሦስት አስርተ ዓመታት ከኢትዮጵያ ሕዝብ በዘረፉት ገንዘብ በዓለማቀፍ ደረጃ ተጽኖ ፈጣሪ ቡድኖችን በከፍተኛ ገንዘብ በመቅጠር፣ ደጋፊዎቻቸውን እና ግብረ አበሮቻቸውን በማስተባበር የኢትዮጵያንና ኤርትራን ስም ለማጠልሸት እና የዲፕሎማሲ ጫና ለመፍጠር እያደረጉት ያለውን ጥረት በጽኑ ተቃውመዋል፡፡
የታላቁ የሕዳሴ ግዳብ ድርድርን በተመለከተ ሱዳንና ግብፅ የሚያደርጉትን ኢፍትሐዊ ድርጊት በማውገዝ ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ በሚል ኢትዮጵያ የያዘችውን አቋም አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል፡፡
ሱዳን ዓለም አቀፍ ሕግን በመጣስ የፈፀመችው ወረራ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ፣ ስልጣን የሚያዘው በምርጫ ብቻ መሆኑን በማወቅ ማንኛውም አካል ከጥፋት እንዲቆጠብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተጀመረው ሰላማዊ ወዳጅነት ከምንጊዜውም በላይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፍ እንደሚሰጡም አረጋግጠዋል፡፡
በድጋፍ ሰልፉ ላይ ከኢትዮጵያና ኤርትራዊያን በተጨማሪም የሀገራቱ ወዳጆች ተገኝተው በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ላይ እየደረሰ ያለው ጫና መቆም እንዳለበትና ለዚህም ከሀገሮቹ ጐን እንደሚቆሙ ገልጸዋል፡፡
ሰልፈኞቹ በኢትዮጵያ ላይ እየተካሄደ ያለውን የተዛባ መረጃ መነሻ ያደረገ የስም ማጥፋት ዘመቻ በተመለከተ ለእንግሊዝ መንግሥትና ለሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት መልዕክት ማስተላለፋቸውን አሚኮ በዘገባው አስታውቋል፡፡