ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ለኒጀር ገለፃ አደረገች

ሚያዝያ 28/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ለሆነችው ኒጀር ማብራሪያ ሰጠች።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከኒጀሩ አቻቸው ሞሀመድ ባዞም ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

መሪዎቹ ባደረጉት ውይይት የውሀ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያ የያዘችውን እውነት አስረድተዋል።

ኒጀር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የወቅቱ ተለዋጭ አባል ሀገራት መካከል አንዷ ናት።

የፀጥታው ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ጋር በተገናኘ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን እና በትግራይ ክልል የተደረገውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ በተመለከተ አሳስበውኛል የሚላቸውን ጉዳዮች ሲያነሳ እንደነበር ይታወቃል።

የፕሬዝዳንቷ የኒጀር ቆይታም ኒጀር ኢትዮጵያን በተመለከተ በፀጥታው ምክር ቤት በሚነሱ ጉዳዮች ላይ የተሻለ ግንዛቤ እንድትይዝ አድርጓታል ተብሏል።

በቅርቡ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዶ/ር መሪየም አልሳዲቅ አልመህዲ ግድቡን በተመለከተ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።

በተመሳሳይ ከዚህ ቀደም የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚንሰትር ሳሚ ሹክሪ የግድቡን ድርድር በተመለከተ የአገራቸውን አቋም ለማንጸባረቅ ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገራት ጉዞ አድርገው ነበር።

ኢትዮጵያም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የያዘችውን እውነት እና አቋም ለማንፀባረቅ የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል የኢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡