ኤጀንሲው ሀገራዊ የበይነ መረብ ደህንነት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ረቂቅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተወያየ ነው

ሚያዝያ 28/2013 (ዋልታ) – የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አዲስ ባዘጋጀው ሀገራዊ የበይነ መረብ ደህንነት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ረቂቅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።

ዓለም አሁን ያለችበትን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ደረጃ የሚመጥን የበይነ መረብ ምኅዳር መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ ረቂቁ መዘጋጀቱ ተገልጿል።

በሌላ በኩል የበይነ መረብ ምኅዳሩ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት ያለበት በመሆኑ ሰነዱ ይህን መቋቋም የሚያስችል አሠራር መዘርጋትን ታሳቢ ያደረገ ነው ተብሏል።

ከዚህ ባለፈም የሀገርን ደህንነት ማስጠበቅ እንዲሁም በይነ መረብን በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ዘርፎች መጠቀም እንዲቻል የበይነ መረብ ደህንነትን ማረጋገጥ አስፈላጊ በመሆኑ ምኅዳሩን በጠንካራ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ መደገፍ እንደሚያስፈልግ መገለጹን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።