ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል አገር መሆኗ የኢኮኖሚ ትብብሮችን ከማስፋት ባለፈ ተደማጭነቷ እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል – አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

ነሐሴ 19/2015 (አዲስ ዋልታ) ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል አገር መሆኗ የኢኮኖሚ ትብብሮችን ከማስፋት ባለፈ በዓለም አቀፍ የባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ ተደማጭነቷ እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው 15ኛው የብሪክስ አባል ሀገራት ጉባኤ ኢትዮጵያን ጨምሮ አርጀንቲና፣ ግብጽ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬት የብሪክስ አዲስ አባል አገራት መሆናቸው ይፋ መደረጉ ይታወቃል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗን ተከትሎ ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝ ባለፉት ጊዜያት ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረት ሲካሄድ መቆየቱን መጠቆማቸው ይታወሳል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ 40 አገራት የብሪክስ አባል ለመሆን ፍላጎት ማሳየታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ውስጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ የስድስት አገራት የአባልነት ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን ጠቅሰው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከጉባኤው ቀደም ብሎ ከብሪክስ አባል አገራት መሪዎች ጋር በነበራቸው ውይይት የኢትዮጵያ ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል ነው ያሉት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረኮች ያበረከተችውን አስተዋጽኦ እንዲሁም
በኢኮኖሚው መስክ ያላትን መጻኢ ተስፋ በማሳየት በኩል ጉልህ ሚና አበርክተዋል ነው ያሉት፡፡

ይህም የኢትዮጵያ ጥያቄ በአጭር ጊዜ ተቀባይነት እንዲያገኝ አድርጓል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል አገር መሆኗ የኢኮኖሚ ትብብርና የኢንቨስትመንት አማራጯን እንደሚያሰፋም አምባሳደር ሬድዋን አብራርተዋል፡፡

የብሪክስ መጠናከር በአንድ የመገበያያ ገንዘብ የታጠረውን የዓለም ገበያ አማራጭ እንዲኖረው ዕድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።

ይህም የልማት ፋይናንስ አማራጮችን በማስፋት ኢትዮጵያን ጨምሮ የታዳጊ አገራትን ተጠቃሚነት በማሻሻል በኩል ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በኢኮኖሚና በዲፕሎማሲ እያደገ በመጣው ብሪክስ አባል መሆኗ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተደማጭነት እንደሚያሰፋም ጠቁመዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በበኩላቸው ባለፉት ጊዜያት በተሰሩ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራዎች በዓለም አቀፍ መድረኮች የኢትዮጵያ ተደማጭነት እንዲሰፋ ማድረግ ማቻሉን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ለመሆን ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱም የዚሁ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተከናወኑ ተከታታይ የዲፕሎማሲ ጥረቶች ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ
ሲደርስባት የነበረውን ጫና በመቀልበስ ተቀባይነቷ እንዲጨምር ማድረግ ማቻሉንም ጨምረው መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ለአብነትም በርካታ የአገራት እና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን አንስተዋል፡፡

በቀጣይም የኢትዮጵያ የሁለትዮሸና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ እንዲጎለብት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡