በዚምባብዌ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ኤመርሰን ምናንጋግዋ አሸነፉ

የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ

ነሐሴ 21/2015 (አዲስ ዋልታ) በዚምባብዌ በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የገዥው ዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ መሪ ኤመርሰን ምናንጋግዋ 52 ነጥብ 6 በመቶ ድምፅ በማግኘት አሸናፊ ሆነዋል፡፡

በምርጫው የምናንጋግዋ ጠንካራ ተፎካካሪ የነበሩት የሲቲዝን ኮአሊሺን ፎር ቼንጅ ፓርቲ ተወዳዳሪ ኔልሰን ቻሚሳ 44 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸውን የዚምባብዌ የምርጫ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

የደቡባዊ አፍሪካ የልማት ማህበረሰብ ሳዴክን ጨምሮ በብዙ ታዛቢዎች ዘንድ ምርጫው በብዙ መስፈርቶች ጉድለቶች እንደነበሩበት የተገለጸ ሲሆን በተለይም የምርጫ ጣቢያዎች ዘግይተው መከፈት፣ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ለገዥው ፓርቲ የሚወግን የሚዲያ ሽፋን እንዲሁም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅስቀሳ እንዳያካሂዱ መከልከል የተስተዋሉ ችግሮች እንደነበሩ ተጠቁሟል ፡፡

የተቃዋሚ ፓርቲ ተወዳዳሪዎች ምርጫው የተጭበረበረ ነው በሚል ውጤቱን እንደማይቀበሉና ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወስዱ መናገራቸውን የአልጃዚራ ዘገባ አመላክቷል፡፡

በፈረንጆቹ 2017 ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ስልጣን የተረከቡት ምናንጋግዋ ፕሬዝዳንት ሆነው ዳግም መመረጣቸው የመጨረሻ የስልጣን ዘመናቸው መሆኑም በመረጃው ተጠቅሷል፡፡

ዛኑፒ ኤፍ ፓርቲ አገሪቷ ከቅኝ አገዛዝ በፈረንጆቹ 1980 ነጻ ከወጣች ጀምሮ እየመራ ሲሆን ዚምባብዌን በማያቋርጥ የኢኮኖሚ ቀውስ ከቷታል በሚል ይወቀሳል፡፡