ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን አልምታ የመጠቀም ሙሉ መብት አላት- ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ

ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ

መጋቢት 27/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ በሉዓላዊ ግዛቷ ውስጥ የሚገኘውን የተፈጥሮ ሀብቷን አልምታ የመጠቀም ሙሉ መብት እንዳላት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፖለቲክስና የአፍሪካ ጥናት ማዕከል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ አስታወቁ፡፡

በዓባይ ወንዝ ላይ የተለያዩ ጥናቶችን ያደረጉት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለፁት፣ በዓባይ ወንዝ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ሱዳንና ግብጽ የያዙት አቋም የተሳሳተ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአንፃሩ የራሷን የተፈጥሮ ሀብት ሌሎችን በማይጎዳ መልክ ለመጠቀም የምታደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ማንኛውም ሉዓላዊ አገር ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ያለማንም ከልካይነት አልምቶ የመጠቀም ሙሉ መብት እንዳለው የሚያስረዱት ፕሮፌሰር ተስፋዬ፣ ኢትዮጵያም የዓባይን ውሃ በመገደብ ሌሎችን በማይጎዳ መልክ መገልገል እንደምትችልና ይህን ለማድረግም ሙሉ መብት እንዳላት ገልፀዋል፡፡

የታችኛው ተፋሰስ አገራት ሱዳንና ግብጽ የዓባይ ውሃ አጠቃቀምን በተመለከተ የኢትዮጵያን ጥቅም ባላከበረ መልኩ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ስምምነቶች ማድረጋቸውን አስታውሰው፣ ሁለቱ ሀገራት የውሃውን ድርሻ ተገቢ ባልሆነ መልኩ መከፋፈላቸውን አመልክተዋል፡፡

ክፍፍሉ ዋንኛዋ የውሃው መነሻና 86 ከመቶ የውሃ ድርሻ የምታበረክተውን ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች የላይኛው የተፋሰሱ አገራትን ያላካተተ በመሆኑ የሁለቱ አገራት ስምምነት ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቀዋል፡፡

የግብጽ መሪዎች በተደጋጋሚ “ከድርሻችን አንዲት ጠብታ ውሃ እንዲነካብን አንፈቅድም” ሲሉ መሰማታቸውን የሚገልፁት ፕሮፌሰር ተስፋዬ፣ አገራቱ ድርሻችን የሚሉት የተሳሳተ እሳቤ ውጤት መሆኑን አመልክተዋል፡፡