ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መሪነት ባልተሸረሸረ መልኩ ድርድሩ እንዲቀጥል ፍላጎት አላት- ዶ/ር ስለሺ በቀለ

ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ
መጋቢት 29/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መሪነት ባልተሸረሸረ መልኩ ድርድሩ እንዲቀጥል ፍላጎት እንዳላት የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ገለጹ፡፡
በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መዲና ኪንሻሳ ከመጋቢት 25 እስከ 28/2013 ዓ.ም ድረስ የተደረገውን የሶስቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይና የውሃ ሚኒስትሮች እንዲሁም ቴክኒካዊ ባለሙያዎች ውይይት በተመለከተ መግለጫ የሰጡት ሚኒስትሩ፣ ሱዳንና ግብጽ ድርድሩን የማጓተት ስልት ስለመከተላቸው ተናግረዋል፡፡
የአገራቱ የድርድሩን ቅርጽ የመለወጥ እና ከይዘት ይልቅ ሂደት ላይ ማተኮር በኪንሻሳው ስብሰባ ላይ መንጸባረቁን የጠቆሙት ዶክተር ስለሺ፣ ግብፅ እና ሱዳን የአፍሪካ ህብረት የተሰጠውን የማደራደር ኃላፊነት ወደ ጎን ለማድረግ ሙከራ ማድረጋቸው ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም በሀገራቱ የቀረቡት የሌሎች አደራዳሪዎች ጥሪን ኢትዮጵያ የማትቀበለው መሆኑን በመግለጽ፣ ግብፅ ለሱዳን ከታዛቢዎች ጋር የተያያዙ እና የድርድሩን ቅርጽ የመለወጥ እንቅስቃሴዎች የሰጠችው ድጋፍ ተቀባይነት የሌለው ስለመሆኑ በመግለጫው ተመልክቷል፡፡
ታዛቢ ተብለው የተመረጡ ደቡብ አፍሪካ፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት እየተጫወቱት ያለው ሚና ታሳቢ በማድረግ እንዲቀጥሉ ስምምነት ላይ መደረስ መቻሉን አመላክተዋል፡፡
በቀጣይ የስምምነት ሂደት የህብረቱ መሪ የመሪነት ሚናቸው ባልተሸረሸረ መልኩ ድርድሩ እንዲቀጥል ፍላጎት እንዳላትም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ከግድቡ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ጋር በተያያዘ መረጃዎችን ለመለዋወጥ ዝግጁ መሆኗን በመግለጽ ሙሌቱ በተያዘለት ጊዜ እንደሚካሄድ አስረድተዋል።
ሃገራቱ የሚያደርጉት የሶስትዮሽ ድርድር አደራዳሪዋ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት በሚያስቀመጡት የጊዜ ገደብ አልያም በሚያደርጉት ጥሪ መሰረት የሚከናወን እንደሆነ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
(በሰለሞን በየነ)
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛው የፌስቡክ ገፃችን
https://www.facebook.com/waltainfo
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ
የቪዲዮ መረጃዎቻችንን ለማግኘት ትክክለኛውን የዩቲዩብ ቻናላችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛው የትዊተር ገፃችን
አብራችሁን ስለሆናችሁ ደስተኞች ነን!