ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ችግር አስወግዳ ሰላሟን ታረጋግጣለች

ኅዳር 12/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ ሃይሎች የጋራ ጥምረት የተጋረጠባትን አደጋ አስወግዳ ሰላምና ደኅንነቷን ታረጋግጣለች ሲሉ ዴንማርካዊው ፕሮፌሰር ቶቢያስ ሃግማን ተናገሩ።
ኢትዮጵያን የተመለከቱ በርካታ መጽሃፍትን የጻፉት ፕሮፌሰር ቶቢያስ ሃግማን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ አሁን የተጋረጠባትን አደጋ አልፋ ሰላምና ደኅንቷን ማረጋገጥ ትችላለች የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ከፍተኛ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለው በመሆኑ በአሸባሪው ህወሓት የተደቀነውን አደጋ መቀልበስ እንደሚችል ተናግረዋል።
አሁን ኢትዮጵያ የገጠማት ችግር ሊቢያ፣ የመንና ሶሪያ ካጋጠማቸው ችግሮች ይለያል ያሉት ፕሮፌሰሩ የኢትዮጵያ ችግር የሚቀለበስ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥትም ከእነዚህ አገራት በተቀራኒው ሕጋዊና ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለው እንዲሁም አቅም ያለው መንግሥት መሆኑን ነው ያስረዱት።
ኢትዮጵያ እንደሌሎቹ አገራት ቅኝ ያልተገዛች አገር መሆኗም ለየት እንደሚያደርጋትና ይህም ኢትዮጵያ በቀላሉ ወደ ቀድሞ ሰላሟ እንደምትመለስ ያስችላታል ብለዋል።
የኢትዮጵያን መንግሥት መደገፍ የሚገባቸው የውጭ ሃይሎች በተቃራኒው አሸባሪውን ህወሓት መደገፋቸውን ገልጸው ይህም ሊስተካከል እንደሚገባ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰላም ማምጣት ከተፈለገ የኢትዮጵያን መንግሥት መደገፍና ማገዝ ይገባል ነው ያሉት።
አሸባሪው ሕወሓት ሥልጣን ላይ በነበረበት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እየፈጸመ መቆየቱንም አስታውሰዋል።
ይሁንና ምዕራባውያኑ የቡድኑን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ወደ ጎን በማለት ለቡድኑ ድጋፍ ማድረጋቸው ተገቢ አለመሆኑን አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ምዕራባውያኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አጀንዳ ለማወቅ ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው ብለዋል።
በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ግን የምእራባዊያኑ አካሄድ መቀየሩን ጠቁመው ለዚህም አሸባሪው ህወሓት ከውጭ ሃይሎች ጋር ያለውን ቁርኝት በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
አሸባሪ ሕወሓት ከእነዚህ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አባላት ጋር ያለውን ወዳጅነት በመጠቀም የተሳሳተ መረጃ በማስተላለፍና የመንግሥት ስም እንዲጠለሽ እየሰራ ይገኛል።
የሐሰት ትርክቱን ለመቀየርና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያለውን እውነታ ለማስገንዘብ የኢትዮጵያ መንግሥት የዲፕሎማሲ ሥራውን ማጠናከር እንዳለበት ፕሮፌሰር ቶቢያስ ተናግረዋል።
ምዕራባውያን አገራት በአፍሪካ የውስጥ ጉዳይ የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት የአገራቱን ሉዓላዊነት የሚያኮስስ መሆኑን ጠቁመው ኢትዮጵያ ይህንን መፍቀድ እንደሌለባት አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ታሪክም ቅኝ ገዥዎችን በማንበርከክ ነጻነቷን አውጃ የዘለቀች አሁንም በዚሁ የምትቀጥል ሉአላዊት አገር መሆኗን ገልጸዋል።