ህብረተሰቡ ሳይዘናጋ የኮቪድ-19 ክትባትን ሊወስድ እንደሚገባ ተገለጸ

ኅዳር 12/2014 (ዋልታ) ህብረተሰቡ ባልተገባ ወሬ ሳይዘናጋ የኮቪድ 19 ክትባትን በመውሰድ እራሱን ከበሽታው ሊጠብቅ እንደሚገባ የጅማ ዩኒቨርሲቲ አሳሰበ።
በጅማ ከተማ ከነገ ጀምሮ ለ34 ሺሕ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም እንደ ጅማ ዞን በሚቀጥሉት 10 ቀናት ለ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት እንደሚሰጥ ተመላክቷል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ የአደጋ ጊዜ ትግበራ ማእከል የቫይረሱን ስርጭትና የክትባቱ አሰጣጥ ተግዳሮትን በማስመልከት ትላንት የውይይት የመድረክ አካሂዷል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና ሀኪም ፕሮፌሰር ኢሳያስ ከበደ በወቅቱ አንዳሉት ከኮቪድ 19 ክትባት ጋር ተያይዞ የሚነገሩ ያልተገቡ ወሬዎች ህብረተሰቡን እያዘናጉ ነው።
ከክትባቱ ጋር በተያያዘ የሚናፈሱ ያልተረጋገጡ ወሬዎች ህብረተሰቡ ክትባቱን በጥርጣሬ አንዲመለከተው ያደረገው መሆኑን ጠቁመው ህብረተሰቡ ባልተገቡ ወሬዎች ሳይዘናጋ ክትባቱን በመውሰድ እራሱን ከበሽታው ጥቃት እንዲጠብቅ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።