ኤጀንሲው የኅብረት ሥራ ማኅበራት ኢግዚብሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም አስጀመረ

ግንቦት 17/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ከተማ ዐቀፍ የኅብረት ሥራ ማኅበረት የመጀመሪያውን ኢግዚብሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም “የኅብረት ሥራ ማኅበራት ግብይት ለተረጋጋ የገበያ ሥርዓት” በሚል መሪ ሃሳብ በይፋ አስጀምሯል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው አሊ መርኃ ግብሩ የግብይት ድርሻን ለማሳደግ፣ ሀገሪቱ ከተጋረጠባት የኢኮኖሚ ጫና ለመውጣት እና ኅብረት ሥራ ማኅበራት እንደ ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ለዘላቂ ሰላም እና የተረጋጋ ገበያ እንዲሰፍን ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኅብረት ሥራ ማኅበራት የማኅበረሰብ የሥራ ሁኔታና የኑሮ ውድነትን በማሻሻል ለዘላቂ ሰላም  መስፈን የሚያደርጉትን ጥረት በማጠናከር በአምራች እና በሸማቾች መካከል ዘላቂ የጋራ  ተጠቃሚነትን ማስፈን እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ አደም ኑሬ በበኩላቸው የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የሁሉም ርብርብ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው ገበያን ለማረጋጋት የተጀመረው የእሁድ ገበያ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

የኅብረት ሥራ ግብይት በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ለ100ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ14ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል፡፡

በአመለወርቅ መኳንንት