ከ200 በላይ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት የንግድ ትርዒት ሊካሄድ ነው

ግንቦት 17/2014 (ዋልታ) ከ200 በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት የኢትዮ ቻምበር ዓለም ዐቀፍ የንግድ ትርዒት በኢግዚብሽን ማዕከል ሊካሄድ ነው።

በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተዘጋጀው 12ኛው የኢትዮ ቻምበር ዓለም ዐቀፍ የንግድ ትርዒት ከግንቦት 25 እስከ 29 ቀን 2014 ዓ.ም ይካሄዳል ተብሏል።

የንግድ ትርዒቱ ምርትና አገልግሎትን ለማስተዋወቅ፣ የሥራ እድል ለመፍጠር፣ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር የገበያ ትስስር እንዲሁም የቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር ለማድረግ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተነግሯል፡፡

በተጨማሪም ለሀገር ምርት ቅድሚያ በመስጠት የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ሚናው የጎላ ነው ተብሏል።

ከንግድ ትርዒቱም ባለፈ የንግድ መድረክ ላይ ከ50 በላይ ከንቲባዎች ከግሉ ዘርፍ ጋር የሚወያዩበት ይሆናልም ነው የተባለው፡፡

የንግድ ትርዒቱ “የኢትዮጵያን ይግዙ፤ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ” በሚል መሪ ሃሳብ ይካሄዳል፡፡

በትዕግስት ዘላለም