ከቡልጋሪያ እስከ ሳይንስ ሙዚየም…….

የዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ መሐመድ ሀሰን

“ወደዛ የምትጓዙ ሁሉ ተስፋ ማድረግ ጀምሩ” – ጋዜጠኛ መሀመድ ሀሰን

 

ዓለም በብዙ ነገር አርአያ የሚያደርጋት ጀርመን 50 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎቿን የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ ወደ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ታስገባለች፡፡ በእውቀትም በክህሎትም በጣም የዳበሩ ዜጎች አሏት ተብሎ የሚታሰበው ደቡብ ኮሪያ፤ ከ69 በመቶ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎቿ የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ይህን ስልጠና ትሰጣለች፡፡ እነ ጀርመን ላይ ያመጣውን ለውጥ ያየችው አሜሪካም በአመት በዩኒቨርስቲዋ በኩል ከ25 ሺሕ እስከ 44 ሺሕ ዶላር እያስከፈለች የቴክኒክና ሙያን ትምህርት ታስተምራለች፡፡ ሀገራቱ የቴክኒክና ሙያ ትምህርቶችን መስጠት ያስፈለጋቸው የተማሪዎችን ክህሎት በማሳደግ ላይ ያላቸው ሚና ሰፊ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህም የሰለጠኑ ሀገራት እኚህ ዓይነት ትምህርቶችን በመስጠት በፈጠራዎች፣ ስታርት አፖች እና ቴክኖሎጂዎች ላይ በስፋት እየሰሩበት ይገኛሉ፡፡

 

ወደ አፍሪካ እንምጣ…. ከሳህራ በታች ያሉ ሀገራት ላይ ያለው ሥራ ፈላጊ ሀይል 80 ከመቶ ስራውን የሚፈጥረው በዚሁ በስታርት አፕ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ የአፍሪካ ልማት ባንክ ከአፍሪካ አጠቃላይ ምርት ውስጥ 55 ከመቶ ድርሻውን አሁንም ለስታርት አፕ ይሰጣል፡፡ በዘመኑ ልክ መፍጠን፣ በክህሎት መዳበር፣ ፈጠራ ላይ ትኩረት ማድረግና ስታርት አፕን ማበረታታት የአህጉሪቱ የችግር መውጫ መንገድ መሆኑ ይታመናል፡፡

 

ኢትዮጵያስ?

10 አመት ወደ ኋላ… “በትልቁ ማሰብ፤ ከትንሹ መጀመር” የሚል የማይናወጥ አቋም ያላቸው የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እየተመራና እሳቸውም በተሳተፉበት ቡድን ውስጥ ቴክኖሎጂን የማዘመን፣ ስታርት አፕን የማስፋፋት እና ዘመንን የመምሰል ስራዎችን ይሰራ ነበር፡፡ ቡልጋሪያ ከሚገኘው የያሬድ አረጋዊ ህንፃ ላይ ሆኖ፡፡

ነገር ግን ጅማሮውን እንደ ቅዠት ሀሳቦችን እንደ ተረት ይቆጥሩ የነበሩ በርካቶች በሙከራው ተሳልቀዋል፤ ጅማሮውን ንቀዋል፡፡ መነሻው ራዕይ መንገዱ ፅናት የነበረው ይህ ስራ ግን “በአትችሉም” የቃላት እንቅፋት ወድቆ የሚቀር አልነበረም፡፡ የብዙ ተቋማት ዲጂታላዜይሽን ስራዎችን ከመከወን አንስቶ፣ ሶፍትዌሮችና አፕሊኬሽኖችን በማበልፀግ ዘመናዊነትን ለኢትዮጵያ ያስፋፋ ጀመር፡፡ በዚህ የተጀመረው ተግባርም የነዳጅን መኪናን ወደ ኤሌክትሪክ በመቀየር የመጀመሪያው ቢሮ መሆን ቻለ፡፡ ብዙዎችንም ጉድ አስባለ!

 

እንዲህ እንዲህ እያለ 10 አመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ጉዳዩ የታዳጊዎች ትኩረት ሆነ፡፡ በአንድ መሪ የተጀመረው ይህ እንቅስቃሴ የወጣቱ ተስፋ ወደ መሆን ከፍ አለ፡፡ እንደ ሀገር ትኩረት ሆነ፡፡ ከቡልጋሪያ የተነሳው ጉዞ በአሮጌው ቄራ አቆራርጦ አራት ኪሎ ደረሰ፡፡ ሳይንስ ሙዚየምንም ገነባ፡፡ በሀገሪቱ ሳይንቲፊቲክ አስተሳሰብ እንዲፈጠር የነበረው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ህልምም እውን ሆነ፡፡ ትውልዱ እንዲያነብና እንዲጠይቅ አብርኆትን ተቸረው፡፡ ሌሎች ብዙ…….

 

አሁን ስታርት አፕ በኢትዮጵያ የፈጠራ አውድ ሆኗል፡፡ የወጣቱ ተስፋ፣ የማህበረሰቡም ችግር መፍቻ ቁልፍ መሆን ችሏል፡፡ ቴክኒክና ሙያ ላይ የነበሩ ልጆች በሳይንስ ሙዚየም የተከፈተው ኤግዚቢሽብን ላይ ቀርበው ሚሊየን ብር የሚሸጡ ሀሳቦችን እያቀረቡ ነው፡፡ ሚሊየን ብሮች ማግኛ ሆኗል፡፡ አሁን ስታርት አፕ በኢትዮጵያ እንደሚፈስ ታሪክ ሆኗል፡፡ ትውልድ እየተቀባበለው የሚቀጥል የእውቀት ዥረት፡፡ አሁን ስታርት አፕ በኢትዮጵያ በዙሪያ ያሉ ችግሮችን በመቃኘት ቴክኖሎጂካዊ መፍትሔ ሰጪ ሆኗል፡፡ በየሰፈሩ ቁጭ ብለው የነበሩ ሀሳቦች መራመድ ጀምረዋል፡፡ ሳይንስ ሙዚየምም የታዳጊዎች ቤት ሆኗል!

 

በእርግጥ ይህ አይነት ክህሎት የሚዳብርበት የቴክኒክና ሙያ ትምህርት በሀገራችን የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ክህሎታችንን የሚያሳድገውን የቴክኒክና ሙያ ትምህርት እየናቅን ፣ “ቀለሜ” ብቻ የሚኮንበትን የምዕራባዊያን ንድፈ ሐሳብ (ቲዮሪ) ላይ መመስረት ልክ አይደለም፡፡ የትምህርት ስርዓታችን ዲግሪ ብቻ ከማሸከም አለፍ ብሎ በቂ ኢንቨስት በማድረግ ይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ሥራዎች ከዚህም በላይ መሰራት አለባቸው፡፡ “ቴክኒክና ሙያ” የሚለውን ቃል በትክክል እንድረዳው ከማድረግ አንስቶ!

 

ሚዲያዎችም ቢሆኑ በዚህ በስታርት አፕ ኤግዚብሽን ውስጥ ተሳታፊ መሆን አለባቸው፡፡ ያለ ቴክኖሎጂ እርዳታ ከዘመኑ ጋር መፍጠን አይቻልምና፡፡

 

በመጨረሻም ከፈጠራ አስተሳሰቦችና ቴክኖሎጂካዊ ግኝቶች ጋር እየቀረበ የመጣውን ትውልድ ሂዱና ሳይንስ ሙዚየም ተመልከቱት፡፡ እዛ ብዙ ግኝቶች አሉ፡፡ ማኅበረሰቡን እፎይ የሚያስብሉ መፍትሔዎች በብፌ ቀርበዋል፡፡ ሀሳቦችን የሚፈጥሩላችሁ ሀሳቦች ዳር እስከ ዳር ሞልተዋል፡፡ ከዳንቴ ዲቫይን ኮሜዲ ንግግር ተወስዳ በጋዜጠኛ መሐመድ ሀሰን በተቀየረች በአንድ አባባል እንሰናበት፡፡ “ወደዛ የምትጓዙ ሁሉ ተስፋ ማድረግ ጀምሩ”! ሰላም፡፡

 

(ከዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ መሐመድ ሀሰን ቃለ ምልልስ የተወሰደ)

 

በሳሙኤል ሙሉጌታ