ከቡና ልማት ተጠቃሚ ለመሆን መትጋት እንደሚገባ ተጠቆመ

ሰኔ 28/2014 (ዋልታ) ከቡና ልማት ተጠቃሚ ለመሆን መትጋት እንደሚገባ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር እርስቱ ይርዳው አሳሰቡ።

ርዕሰ መስተዳደር እርስቱ ይርዳው እና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በጌዴኦ ዞን የቡና ችግኝ ተከላ አካሂደዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ በዚህ ወቅት እንደገለጹት የጌዴኦ ዞን በኢትዮጵያ ደረጃ በቡና ምርቱና በጥምር ግብርናው የሚታወቅ ነው፡፡ ለዚህም የዞኑ ቡና አብቃይ አርሶ አደሮችን ህይወት ለመቀየር በትኩረት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዞኑ አርሶ አደሮች በቡና፣ በዛፍ ልማትና በጥምር ግብርና እያደረጉት ለሚገኘው ጥረት ምስጋና አቅርበው የአርሶ አደሮቹ ህይወት እንዲቀየር የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን እገዛ ያደርጋል ነው ያሉት።

ቡናን በጥራት ለገበያ ለማቅረብ የተያዘው እቅድ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ጠቁመው በአረንጓዴ አሻራ ከሚተከለው አንድ ቢሊየን የችግኝ መካከል 80 ሚሊየን የሚሆነው የቡና ችግኝ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል፡፡

የጌዴኦ ዞን በ70 ሺሕ ሄክታር ላይ ቡና እየለማ መሆኑ ታውቋል።