የከተሞች የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በለገጣፎ ለገዳዲ ተካሄደ

ሰኔ 28/2014 (ዋልታ) “አሻራችን ለከተሞቻችን ለትውልድ እንስራ ፤ ለኢትዮጵያ እንትከል” በሚል መሪ ሀሳብ የኢትዮጵያ ከተሞች የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ተካሂዷል።

በመርኃ ግብሩ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ትላንት የነበሩ ክፍተቶችን ለመሙላት ዛሬን በመስራት ለገነ የተሟላች ሀገርን ማስረከብ ይኖርብናል ብለዋል።

በዓለም ዐቀፍ ደረጃ እየጨመረ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመታደግ እየተሰራ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሯ ኢትዮጵያ ለዓለም ከተሞች ተምሳሌት የሚሆን የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር እያካሄደች መሆኑንም ተናግረዋል።

በዘንድሮው የአራተኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከ6 ሚሊየን በላይ ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው ለዚህ ደግሞ ከተሞች ጉልህ ሚና መጫወት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ከተሞችን ፅዱና ምቹ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸው በለተይም የፍሳሽና የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ከተሞች ለአረንጓዴ አሻራ ያላቸው ሚና ለምግብ ዋስትናን ያረጋገጠ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ማስቀጠል ለአየር ንብረት የማይበገር ኢኮኖሚን ማረጋገጥ የሚያስችል መመሪያ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በሳራ ስዩም