ከባድ ውጊያ ላይ ያሉት የሱዳን ተፋላሚዎች የተኩስ አቁም ድርድር ዛሬ ሊጀምሩ ነው

ግንቦት 6/2015 (ዋልታ) ከባድ ውጊያ ላይ ያሉት የሱዳን ተፋላሚዎች የተኩስ አቁም ድርድር ዛሬ ሊጀምሩ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

ዛሬ መልሶ ይጀመራል ተብሎ ከሚጠበቀው የተኩስ አቁም ንግግር ቀደም ብሎ በዋና ከተማዋ ካርቱም እና በሌሎች ከተሞች ከባድ ውጊያዎች መቀጠላቸው ተገልጿል።

በሱዳን ሠራዊት እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል እየተካሄደ ያለው ውጊያ አንድ ወር ሊሆነው የተቃረበ ሲሆን ተፋላሚዎቹ በሳዑዲ አረቢያ እና በአሜሪካ አደራዳሪነት ለቀናት ድርድር ካደረጉ በኋላ ባለፈው ሐሙስ “ለድርድሩ ተገዢ ለመሆን” ስምምነት ፈርመዋል።

በዛሬው ዕለት ደግሞ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ በሳዑዲዋ የወደብ ከተማ ጅዳ ውስጥ ንግግራቸውን መልሰው ይጀምራሉ ተብሏል።

ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ድርድር ሁለቱ ተቀናቃኝ ኃይሎች ሰላማዊ ሰዎች እና የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቶች ጥቃት እንዳይፈጸምባቸው ጥበቃ ለማድረግ ቢስማሙም ተኩስ አቁም ላይ ግን መድረስ ሳይችሉ መቅረታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

አንድ አሜሪካዊ ዲፕሎማት ድርድሩ እጅግ አስቸጋሪ እና ሁለቱ ወገኖች ለመስማማት ከሚያስችል መቀራረብ ላይ አለመድረሳቸውን እና የተራራቀ አቋም መያዛቸውን ገልጸዋል።

የዛሬው ድርድር ዋነኛው አጀንዳ ተፋላሚዎቹ ተኩስ አቁመው ለዘላቂ ሰላም የሚሆን ንግግር እንዲደረግ መንገድ መክፈት ነውም ተብሏል።