ኮሚሽኑ በሽግግር ፍትሕ ላይ የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ለማስፋት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገለጸ

ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ

ሰኔ 12/2015 (ዋልታ) ለሽግግር ፍትሕ ሂደት ስኬታማነት የሚያግዙ የማኅበረሰብ ግንዛቤ ማስፋት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ገለጸ።

የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ እንደገለጹት በየትኛውም መልኩ የሚከሰት ግጭትና አለመግባባት ዜጎች ለሰብአዊ መብት ጥሰት የመጋለጥ ዕድላቸውን ያሰፋል።

በዚህም አለመግባባቶች የሚከሰትባቸውን ጉዳዮች በመለየት መፍትሔን ማበጀትና ማመላከት ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የሰሜኑን የአገሪቱ ክፍል ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ተከስተው የነበሩ ግጭቶችና አለመግባባቶች ዜጎችን ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መዳረጋቸውን ያነሱት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ለዚህም ብሔራዊ የሽግግር ፍትሕን በማካሄድ የተፈጠሩ ስህተቶችን ማረምን ጨምሮ ስጋቶችንም ማሻሻል የግድ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል ብለዋል።

ይህንን መነሻ በማድረግ እንደ አገር የሽግግር ፍትሕ እንዲካሄድ ምክረ ሃሳብ ካቀረቡ ተቋማትና አካላት መካከል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አንዱና ዋነኛው ስለመሆኑ አስረድተዋል።

በመሆኑም ኮሚሽኑ የሽግግር ፍትሕ ሂደቱን በአግባቡ የማስፈጸምና የመከታተል ኃላፊነት ተጥሎበታል ብለዋል።

ሂደቱ አካታች አሳታፊና ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ እንዲሆን ለማስቻል በቅድሚያ የማኅበረሰብ ግንዛቤ ማስፋት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ በቅንጅት እየተሰራ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

እስካሁን ባለው ሂደትም የሽግግር ፍትሕ አስፈላጊነቱ የአፈጻጸም ሂደቱና ፋይዳውን በሚመለከት የማኅበረሰብ ውይይቶች ተካሂደዋል።

በተደረጉ ሕዝባዊ ውይይቶች ማኅበረሰቡ በሂደቱ ሊካተቱ ይገባል ያላቸውን ምክረ ሃሳብ ለማካተት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።

በተለይም ለሽግግር ፍትሕ አጋዥ የሆኑ ባህላዊ እሴቶችን መጠቀም በውይይቱ ከተመላከቱ ምክረ ሃሳቦች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመው የሽግግር ፍትሕን በሚመለከት እየተዘጋጀ ላለው ፖሊሲ ኮሚሽኑ በግብዓትነት አቅርቦታል ብለዋል።

በቀጣይም ፖሊሲውን በማውጣትና በማዘጋጀት እየተሳተፉ ያሉ አካላት የጉዳዩን አስፈላጊነት በመገንዘብ በግብዓትነት የተገኙ ምክረ ሃሳቦችን ማካተት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።