ከተማ አስተዳደሩ ለዋልያዎች 5 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ሽልማት አበረከተ

መጋቢት 24/2013 (ዋልታ) – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለአፍሪካ ዋንጫ ላለፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 5.6 ሚሊየን ብር ማበረታቻ ሽልማት አበረከተ።

ከተማ አስተዳደሩ የኢትዮጵያ ብሄራዊ እግር ኳስ ቡድን ላስመዘገበው ውጤት የላቀ ክብርና አድናቆት እንዳለው ም/ከንቲባ አዳነች አበቤ ገልፀዋል፡፡

ለቡድኑ አባላት በጥረታችሁ ታሪክ ለማስመዝገብ በመብቃታቹህ፤ ለሃገራችሁ የተለየ የመነቃቃት ስሜት ፈጥራችኋልም ብለዋል።

በእግር ኳስ በግል የሚመዘገብ ውጤት የለም ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፣ ውጤት የሚመጣው ሜዳ ላይ በሚጫወቱት ተጫዋቾች ብቻ ሳይሆን፣ አመራሮች፣ አሰልጣኞች፣ ደጋፊዎች እና ሌሎችም በአንድነት ሲሰሩ ብቻ እንደሆነ አብራርተዋል።

አጠቃላይ አምስት ነጥብ ስድስት ሚሊየን ብር ሽልማት የተበረከተ ሲሆን፣ ለስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለእያንዳንዳቸው 40 ሺህ ብር፣ ለፕሬዝዳንቱ ኢሳያስ ጅራ 90 ሺህ ብር፣ ለዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ 200ሺህ ብር፣ ለቡድን መሪ፣ ለቋሚ ተሰላፊ ተጫዋቾች፣ ለግብ ጠባቂ አሰልጣኝ እና ለምክትል አሰልጣኞች ለእያንዳንዳቸው 150 ሺህ ብር እንዲሁም ለተጠባባቂ ተጫዋቾች 100 ሺህ ብር ተበርክቶላቸዋል።

(በሀብታሙ ገደቤ)