ከተማ አስተዳደሩ በሕዝብ መድረክ የተነሱ ወቅታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ ልዩ ዝግጅት አድርጎ ወደ ተግባር መግባቱን ገለጸ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር

መጋቢት 28/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሕዝቡ ጋር ሲደረጉ በነበሩ ውይይቶች ሕዝቡ በግልፅነት ያነሳቸውን በአጭር ጊዜ መመለስ ያለባቸውን አንገብጋቢ ወቅታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ ልዩ ዝግጅት አድርጎ ወደ ተግባር መግባቱን ገለጸ፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ያወጣው ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከህዝቡ ጋር ሲደረጉ በነበሩ ውይይቶች  ህዝቡ በግልፅነት ያነሳቸውን  በአጭር ግዜ መመለስ ያለባቸውን አንገብጋቢ ወቅታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ ልዩ ዝግጅት አድርጎ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡

በየመድረኮቹ ቃል በገባው መሰረት በፍጥነት  በህዝብ መድረኮች የተነሱት አግባብነት ያላቸው በአጭር ግዜ መመለስ ያለባቸውን   ጥያቄዎች በሙሉ አንድ በአንድ ተለቅመው በእቅድ እንዲመለሱ ለማድረግ የቀሪ ሶስት ወራት የአስተዳደሩ እቅድ በመከለስ አመራሩ የማስተባበር እና የመምራት ሃላፊነት ተከፋፍሎ በሚከተለው  አቅጣጫ  ወደ ተግባር ገብቷል፡፡

በዚሁ መሰረት

1-  ከወቅታዊ የኑሮ ውድነት ማቅለል አንፃር የታቀዱትን ተግባራት መከታተልና ውጤታማ ማድረግ ፤ከስራ እድል ፈጠራና በአጠቃላይ ከኢኮኖሚ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን   ም/ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ  የሚያስተባብሩት የሚመሩት ።

2-  ህዝብ በየመድረኮቹ በርካታ ቅሬታ ያቀረበበትን  አገልግሎት በሌብነት : በእጅ መንሻ  እና በደላላ ነው  የሚሰጠው : አመራሩን ለማግኘት እንቸገራለን  የሚባለውን ችግር ለመቅረፍ በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ደግሞ በምክትል ከንቲባ ማእረግ የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ሂክማ ከይረዲን የሚያስተባብሩት የሚመሩት ።

3-  የከተማ ግብርናን ጨምሮ  ከማህበራዊ ጉዳይ  ጋር የተያያዙ ጉዳዮችንና  ከፕሮጀክቶችን መከታተልና ውጤታማ ማድረግን በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ የሚያስተባብሩት የሚመሩት ።

4-  ከቤት ጋር የተያያዙ ቅሬታዎችንና አዳዲስ የቤት አማራጮችን ወደ ተግባር በመቀየር ከቤቶች ጋር የተያያዙ  ጉዳዮችን  በምክትል ከንቲባ ማእረግ :የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ያስሚን ዋሃቢ ረቢ የሚያስተባብሩት የሚመሩት፡፡

5-  በከተማችን በኑሮ ውድነት ለከፍተኛ ችግር ተጋላጭ የሆኑትን ማህበረሰብ በልዩ ሁኔታ ማእድ ከማጋራት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን እንዲያስተባብሩ በምክትል ከንቲባ ማእረግ የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ነጂባ አክመል የሚያስተባብሩት የሚመሩት።

6-   ስርዓት አልበኝነት ከመቆጣጠርና የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ  አንፃር የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ  ዶ/ር ቀነዓ ያደታ የሚያስተባብሩትና የሚመሩት ግብረ ሃይል ወደተግባር ገብቷል::

ከዚሁ ከህዝብ ቅሬታ መፍታት ጋር ተያይዞ ከከተማ እስከ ወረዳ ድረስ በሳምንት ሁለት ቀናት ማለትም እሮብና አርብ ሙሉ ቀን የትኛውም አመራር ከሌሎች ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥቶ ለህዝቡ  አገልግሎት እንዲሰጥ(ለህዝብ አገልግሎት ብቻ የተወሰነ የባለጉዳይ ቀን እንዲሆን) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውሳኔ አስተላልፎ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡

ይህ ህዝቡ ያነሳቸውን አንገብጋቢ ወቅታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ   በምን መልኩ እየሰራን እንደሆነ ለህዝቡ  ግልፅነት  ለመፍጠር እንጂ  ሌሎች የከተማ አስተዳደሩ መደበኛ ስራዎች በታቀደላቸው መሰረት የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡

ስለሆነም ህብረተሰቡ የከተማ አስተዳደሩ የወሰናቸውን ውሳኔዎች  የሚያደርጋቸው ጥረቶች ከግብ እንዲደርስ የተለመደውን ድጋፉን ሳይቆጥብ ሊያበረክትና ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት ሊረባረብ ይገባል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር

መጋቢት 28/2014 ዓ.ም

አዲስ አበባ

 

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW

ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth

ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured

ቲዊተር https://twitter.com/walta_info

አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!