ከተማ አስተዳደሩ የከተራና ጥምቀት በዓላትን በሰላም ለማክበር ከበጎ ፈቃደኞች ጋር ተወያየ

በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፊታችን የሚከበረውን የከተራ እና ጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር በሁሉም ክፍለ ከተሞች ከተውጣጡ 500 በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ጋር ምክክር አድርጓል፡፡

የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማሰተባበሪያ ቢሮ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በዓሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ የበጎ ፈቃድ ስራው መከናወን ባለበት ሁኔታ ላይ ከወጣቶች ጋር ምክክር በማድረግ  አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

በዚህም በጎ ፈቃደኞች በበዓሉ አከባበር ላይ ስለሚኖራቸው ቅንጅታዊ ሚና ከወጣቶች ጋር ምክክር መደጉ ተገልጿል፡፡

የጥምቀት በዓል የአደባባይ በዓል በመሆኑ በርካታ ምዕመናን እና ጎብኝዎች የሚሳተፉበት በመሆኑ በሰላም መጠናቀቅ እንዲችል የአዲስ አበባ  እና የፌደራል ፖሊስ ከሚሰሩት ስራ በተጨማሪ  ወጣቶች ከፀጥታ ኃይል ጋር በመቀናጀት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሰጡ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነውም ተብሏል፡፡

ወጣቶች የከተማዋን ሰላም ለማስጠበቅ ብሎም በከተማዋ የሚከበሩ ኃይማኖታዊ በዓላት ሰላማዊ ሆነው እንዲጠናቀቁ  ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ በበዓሉ ላይ የሚገኙ ታዳሚያን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ወጣቶች የማስተማርና የማስተባበር ስራም እንዲሰሩ ተጠይቋል፡፡

ሀገራዊ የሆኑ በዓላትን የመልካም እሴት መገለጫ እንዲሆኑ ለውጪው አለም ለማስተዋወቅ፣  የበጎ ፈቃድ ተግባራትን በብቃት ለመወጣት እና  በበዓሉም ላይ ህበረተሰቡን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን በምክክር መድረክ ላይ የተገኙት ወጣቶች ገልጸዋል፡፡

በዓሉ  ጃን ሜዳን ጨምሮ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በተለያዩ ስፍራዎች በርካታ የኃይማኖቱ ተከታዮችና ጎብኝዎቸ በተገኙበት የሚከበር በመሆኑ ወጣቱ ከፀጥታ ኃይል ጋር በጋራ በመሆን አገልግሎት ለመስጠትና ፀጥታን ለማስከበር ብሎም የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ለመስጠት እየሰራ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

(በህይወት አክሊሉ)