ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከታዋቂው ኮያንግፖኦክ ዩኒቨርስቲ ፕሬዘደንት ጋር ተወያዩ

ነሐሴ 25/2015 (አዲስ ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በደቡብ ኮሪያ ቹንቾን ከተማ ከሚገኘው ታዋቂው ኮያንግፖኦክ ዩኒቨርስቲ (KNU) ፕሬዘደንት ኪም ሂዎን ያንግ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በሁለቱ እህት ከተሞች መካከል በተደረሰው ስምምነት መሰረት የከንቲባ ነፃ የትምህርት እድል ፕሮግራም (Mayor’s Scholarship Program) ማመቻቸት በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

በዚህም ዩኒቨርስቲው መስፈርት ለሚያሟሉና የተሻለ ውጤት ለሚያስመዘግቡ የአዲስ አበባ ተማሪዎች በከንቲባ የተሰየመ ነፃ የትምህርት እድል ለመስጠት ተስማምቷል፡፡

የከንቲባ ነፃ የትምህርት እድል (Mayor’s Scholarship program) የከተማ አስተዳደሩ የአዲስ አበባ እህት ከተሞች ውስጥ ከሚገኙ ታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በከተማችን ለሚገኙ በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት ለሚያስመዘግቡ ተማሪዎች የነፃ የትምህርት እድል ለመስጠት በከንቲባ አዳነች አቤቤ የተጀመረ እንቅስቃሴ ሲሆን ለከተማዋ ተማሪዎችም መልካም እድል የሚፈጥር እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የሁለቱን ከተሞች የረዥም ዘመን ወዳጅነትን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ያለመ የደቡብ ኮርያ ቹንቾን ከተማ ስኬታማ የስራ ጉብኝታቸውን አጠናቅቀው ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን ከከንቲባ ፅሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡